የክረምት ወቅት ጥገና ሲደረግለት የሰነበተው ወንጂ ስኳር ፋብሪካ ከዛሬ ጀምሮ ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ስኳር የማምረት ሥራውን ይጀምራል።
ሸንኮራ አገዳ ወደ ፋብሪካው የሚያጓጉዙ ማሽነሪዎች እና የፋብሪካው የጥገና ሥራ መጠናቀቁን የወንጂ ስኳር ፋብሪካ ዋና ሥራ አስኪያጅ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ እዩኤል ለላንጎ አረጋግጠዋል።
በሌላ በኩል ስኳር ለማምረት የሚያስችሉ ሸንኮራ አገዳዎች ዛሬ እንደተቆረጡ ገልጸዋል።
በዲዛይን ካፓሲቲው መሠረት የፋብሪካው በቀን ሸንኮራ አገዳ የመፍጨት ዐቅም 6 ሺህ 250 ቶን መሆኑን ገልጸው፥ ያለውን የሸንኮራ አገዳ አቅርቦትና ሌሎች ምክንያቶች ታሳቢ በማድረግ በቀን 4 ሺህ 890 ቶን ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ሥራውን ይቀጥላል ብለዋል።

በዓመት 601 ሺህ 574 ነጥብ 25 ቶን ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት 70 ሺህ 239 ነጥብ 8 ቶን ስኳር እንደሚያመርትም አስገንዝበዋል።
ፋብሪካው በሙሉ ዐቅሙ ሸንኮራ አገዳ መፍጨት እንዲችል በአርሶ አደር ማሳ ተጨማሪ የሸንኮራ አገዳ ማሳ ለማልማት ዕቅድ ተይዞ እየተሠራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የሸንኮራ አገዳዎችን ዝርያ የማሻሻል፣ሸንኮራ አገዳ የመፍጨት፣ ስኳር የማምረት ዐቅምና የጨመቃ ሂደት ላይ ምርታማነትን የሚያሳድጉ ሥራዎች በጥገና ወቅት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።
ለዘንድሮው ስኳር የማምረት ሥራ በአማካይ 13 ነጥብ 9 በመቶ የስኳር ይዘት ያለው የሸንኮራ አገዳ ዝርያ ለፋብሪካው እንደሚቀርብ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
ፋብሪካው በበጋው ወቅት ሸንኮራ አገዳ በመፍጨት ስኳር የሚያመርት ሲሆን፤ በቀሪዎቹ ወራት በሚኖረው ዝናብና ተፈጥሯዊ ሁኔታ ስለማያመርት ጥገና እንደሚደረግለት ይታወቃል።