AMN ሚያዝያ 15/2018 ዓ.ም
150 አምራቾችና አገልግሎት አቅራቢዎች የተሳተፉበት 27ኛው አዲስ ቻምበር ዓለም አቀፍ ንግድ ትርዒት በኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፍቷል፡፡
የንግድ ትርኢቱ በተለያዩ የቢዝነስ ዘርፎች የተሰማሩ የሀገር ውስጥና የውጪ 150 ተሳታፊዎች ምርትና አገልግሎታቸውን እንዲያስተዋውቁ እና እንዲሸጡ እድል የፈጠረ ነው፡፡
የንግድ ትርኢቱ የንግድ ለንግድ ግንኙነት ለመጀመር፣ ልምድ ለመቅሰም፣ ለድንበር ተሻጋሪ ሽርክና፣ ለፈጠራ እና ለዘላቂ የኢኮኖሚ እድገት ለመፍጠር ያለመ ስለመሆኑ ተገልጿል፡፡
የአዲስአበባ ከተማ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ በመክፈቻ መርሐግብሩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት አዲስአበባ ለንግድና ኢንቨስትመንት ምቹ ከተማ እየሆነች መጥታለች ብለዋል።

የንግድና ዘርፍ ማህበራት ከተማ አስተዳደሩ ትልቅ ትኩረት ከተሰጣቸው ዘርፎች መካከል መሆናቸውን የገለፁት ምክትል ከንቲባው የንግድ ትርኢቱ መዘጋጀት ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዲስፋፋ የበኩሉን አስተዋጾ ያበረክታል ብለዋል።
ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማረጋገጥ የግል ዘርፉ ያለው ሚና የማይተካ ነው ያሉት አቶ ጃንጥራር በዚህም መንግስት ለግሉ ዘርፍ ልዩ ትኩረት እንደሰጠው ተናግረዋል።
የአዲስአበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ምክርቤት ፕሬዝዳንት ወ/ሮ ዘሀራ መሀመድ በበኩላቸው መድረኩ የአገር ውስጥ የንግድ ተቋማትን ከዓለም አቀፍ ገበያ ጋር ለማስተሳሰር፣ አዳዲስ የፈጠራ ሃሳቦችን ለማፍለቅና ዘላቂ ሽርክናዎችን ለመመሥረት እንደ ድልድይ ሆኖ ያገለግላል ብለዋል።

“ዘላቂ ንግድ፤ የንግድ ተወዳዳሪነት በኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል የተከፈተው 27ኛው አዲስ ቻምበር አለም አቀፍ ንግድ ትርዒት እስከ ሚያዚያ 17 ቀን 2018 ዓ.ም ድረስ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ይካሄዳል
በደሳለኝ ሙሐመድ