የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ የሀገሪቱን የፋይናንስ ስርዓት በማሳለጥ የጎላ ሚና እንዳለው የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ፡፡
ከዛሬ ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ ቀናት የሚካሄደው ሁለተኛው ቀጣናዊ የካፒታል ገበያ ጉባኤ በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል መካሄድ ጀምሯል።
የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚህ ወቅት እንዳሉት፤ የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን መፃኢ የፋይናንስ ስርዓት የሚያሳልጥ መሰረታዊ ጉዳይ ነው።
ኢትዮጵያ አካታች የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ በማድረግ በሁሉም ዘርፎች ተጨባጭ ውጤት እያስመዘገበች ትገኛለች ብለዋል።
ማሻሻያው ወደ ተሟላ ትግበራ ከገባ ወዲህ ማክሮ ኢኮኖሚውን በማረጋጋት ሁሉን አቀፍ ዕድገት ማረጋገጥ በሚያስችል ሂደት ላይ መሆኑን ገልጸዋል።
የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙን ተከትሎ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሀገር ውስጥ ገቢን በማስፋት ዕምርታዊ ለውጥ መመዝገቡንም ገልጸዋል።
በኢኮኖሚ ሪፎርሙ መሰረት ወደ ሥራ የገባው የኢትዮጵያ ካፒታል ገበያ ባለስልጣን የኢትዮጵያን የፋይናንስ ስርዓት በማሳለጥ ቁልፍ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።
በመንግሥት የልማት ድርጅቶች ላይ ሪፎርም መደረጉን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ የግሉን ዘርፍ ተሳትፎ የሚያሳድግ ምቹ የኢንቨስትመንት ምህዳር መፍጠር ተችሏል ብለዋል።
ሪፎርሙ ግልጽነትን በመፍጠር፣ በማዕከላዊ ባንክ ላይ ብቻ የተመሰረተውን የፋየናንስ ስርዓት በመቀነስ እና የታክስ መሰረቱን በማስፋት የሚታይ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል፡
፡
የካፒታል ገበያ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ለኢኮኖሚያዊ ሽግግር ወሳኝ መሆኑን አንስተው፤ ለኢትዮጵያ የፋይናንስ ስርዓት ዝማኔ ቁልፍ መሳሪያ ሆኖ እንደሚያገለግል ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ ተዓማኒና ለግሉ ዘርፍ ተስማሚ የፋይናንስ ምህዳር ለማስፈን በተቋማት መካከል ጠንካራ ትብብር መፍጠር እንደሚገባ አመልክተዋል፡፡
በአግባቡ የተደራጀ እና የተሟላ መሰረተ ልማት ያለው የካፒታል ገበያ ስርዓት የኢትዮጵያን የፋይናንስ ዘርፍ ለማሳደግና ከዓለም የፋይናንስ ተቋማት ጋር ለማስተሳሰር ያግዛል ማለታቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የካፒታል ገበያ የኢትዮጵያን መሰረተ ልማት በተለያዩ የቦንድ ኢንቨስትመንት አማካይነት ወደ ሀብት መቀየር የሚያስችል ዕድል መፍጠሩንም ገልጸዋል፡፡