ቢሮው ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ በግብር ከፋዮች ከባለሙያዎች ስነ ምግባር ጉደለት ጋር በማያያዝ የሚቀርቡ ቅሬታዎች በተሟላ ደረጃ ለመቅረፍ የሚያስችል ቴክኖሎጂ አልምቶ ወደ ተግባር ማሸጋገሩ ተገለጸ ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ ቢኒያም ምክሩ በደረሰኝ ቁጥጥር ባለሙያዎች ዩኒፍርም ላይ በተገጠመ የካሜራ ቴክኖሎጂ ፣ ቢሮው ፍትሃዊ የገቢ አሰባሰብ ለመዘርጋት በቀየሳቸው አሰራሮች፣ በቅሬታ አቀራረብና አፈታት እንዲሁም በተቋሙ የሪፎርም ስራዎች ትግበራ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
ቢሮው ለከተማዋ ልማት የሚውል ገቢ በፍትሃዊነት ለመሰብሰብ እንዲሁም በግብር ከፋዮች ከታክስ ውሳኔ ጋር በተያያዘ የሚነሱ ቅሬታዎች ለመፍታት 24 የሚደርሱ አሰራሮች በመዘርጋት ወደ ተግባር ለማሸጋገር መቻሉ በመግለጫቸው ጠቁመዋል፡፡
ከዚህ አኳያ ቢሮው የደረሰኝ የቁጥጥር ተግባራት ከሌብነትና ብልሹ አሰራር የፀዳ ለማድረግ እንደሚያስችል የታመነበት የካሜራ ቴክኖሎጂ ከኢንሳ ጋር በመቀናጀት አልምቶ ወደ ተግባር ማሸጋገሩን በመጠቆም ቴክኖሎጂው የቁጥጥር ባለሙያዎች ቁጥጥራቸውን በድምፅ በምስል በመቅረፅ በቀጥታ ለዋና መስሪያ ቤትና ለቅርንጫፎች እንደሚልክም አብራርተዋል፡፡
ይህም በግብር ከፋዮች ‹‹አለአግባብና ኢ-ፍትሐዊ በሆነ ሁኔታ ቅጣት ተጣለብን፣ የቁጥጥር ባለሙያዎች ጉቦ እየተቀበሉ ነው›› በሚልና በመሳሰሉ መንገዶች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን በማጣራት ትክክለኛ ምላሽ ለመስጠትና የተጠያቂነት ስርዓት ለማስፈን እንደሚያስችል ገልፀዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የቁጥጥር ባለሙያዎች በተፈቀደላቸው አካባቢ ብቻ ቁጥጥር እያደረጉ ስለመሆኑ እንዲሁም ከግብር ከፋዮች ጋር ያላቸው ግንኙነት በድምጽና በምስል በመቅረጽ በዋና መስሪያ ቤት ለመከታተል የሚያስችል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡
በአሁኑ ወቅትም ቢሮው ከደረሰኝ ቁጥጥር ጋር በተያያዘ የበር ለበር ፣ የመጋዘንና የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ላይ ትኩረት በማድረግ በከተማዋ በሁሉም አካባቢዎች ቁጥጥሩን አጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል፡፡
ከቅሬታ አቀራረብና አፈታት ጋር በተያያዘም ቢሮው በተለይም በግብር ከፋዮች ከታክስ ውሳኔ ላይ የቀረቡ ቅሬታዎች በቅሬታ የስራ ክፍሉ በማጣራት ምላሽ እየሰጠ መሆኑን ያነሱት ኃላፊው በዚህም ባለፈው ዓመት ብቻ 63 በመቶ የሚደርሱ የታክስ ቅሬታዎች በማሻሻል ውሳኔ መስጠቱን ተናግረወል፡፡
በሌላ በኩልም በተለያዩ ምክንያቶች ዝቅ ብለው ተወስነው የነበሩ የታክስ ውሳኔዎች በኦዲት ጥራት አረጋጋጭ የስራ ክፍሉ ዳግም ኦዲት በማድረግና በማሻሻል የመንግስት ጥቅም ለማስጠበቅ መቻሉ በጋዜጣዊ መግለጫው አመላክተዋል፡፡
በቅርቡ ደግሞ በቢሮው በሚሰጡ የታክስ ውሳኔ ቅሬታ ውሳኔዎች ያልረካ ግብር ከፋይ እንዲሁም ከአገልግሎት አሰጣጥና ከባለሙያዎች ስነ ምግባር ጋር በተያያዘ ቅሬታ ያለው ማንኛውም ግብር ከፋይ ቅሬታውን በክብርት ከንቲባ ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ለተቋቋመ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ጭምር በማቅረብ እንዲፈታለት ለማድረግ የሚያስችል አሰራር የተመቻቸ መሆኑንም አብራርተዋል ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በፍትሃዊነት ከሚሰበስበው ገቢ 72 ከመቶው ለከተማዋ ሁለንተናዊ ልማትና ብልፅግና፣ ለሰው ተኮርና ድህነት ቅነሳ ፕሮጀክቶች እንዲሁም ለኮሪደር ልማት ስራዎች በቀጥታ እያዋለ ይገኛል ያሉት አቶ ቢኒያም ይህ የከተማ አስተዳደሩ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ግብር ከፋዩ እቃዎችን ሲሸጡና ሲገዛ በደረሰኝ ብቻ እንዲፈፅሙ እንዲሁም ሕብረተሰቡ እቃዎችና አገልግሎቶች ሲገዛ ደረሰኝ በመቀበል የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
በፂዮን ማሞ