በህፃናት አስተዳደግ ላይ የተደቀነ “ድምፅ አልባ” ስጋት

You are currently viewing በህፃናት አስተዳደግ ላይ የተደቀነ “ድምፅ አልባ” ስጋት

AMN – ሚያዝያ 19/2018 ዓ.ም

በአሁኑ ወቅት በከፍተኛ ሁኔታ እየተስተዋለ ያለው የህፃናት እና የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ቁርኝት፤ ወላጆችን ለከፍተኛ ስጋትና ለስነ-ልቦና ውጥረት እየዳረገ እንደሚገኝ ተገለጸ።

የህግ እና የማህበራዊ ጉዳይ አማካሪዋ መቅደስ አስፋው ለኤ ኤም ኤን ዲጅታል እንደገለጹት፤ በቴክኖሎጂው ምጥቀት ሳቢያ የተፈጠረው የዲጂታል ትውልድ ክፍተት በወላጆች እና በልጆች መካከል ያለውን የግንኙነት መስመር አዳጋች አድርጎታል።

አማካሪዋ አክለውም፤ የአሁኑ ትውልድ ገና ከጅምሩ በቴክኖሎጂ ስርአት ውስጥ የሚፈልቅ “ዲጂታል ኔቲቭ” ሲሆን፣ ወላጆች ደግሞ ቴክኖሎጂውን በሂደት የተቀላቀሉ “ዲጂታል ኢሚግራንት” መሆናቸውን ይጠቅሳሉ።

ይህ መሰረታዊ ልዩነት ወላጆች ልጆቻቸውን በጤናማ መንገድ ለመምራት በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ዋነኛ ማነቆ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ልጆች ከጊዜ ወደ ጊዜ ለስልክ እና ለተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያዎች ያላቸው ጥገኝነት አስጊ ደረጃ ላይ መድረሱን የጠቆሙት አማካሪዋ፤ መሳሪያዎቹ የሚያቀርቧቸው ሳቢ ምስሎች እና ድምጾች የህፃናትን አእምሮ በቀላሉ እንደሚቆጣጠሩ ገልጸዋል።

ይህም ህፃናት ለተፈጥሯዊው አካባቢያቸው ደብዛዛ ስሜት እንዲኖራቸውና ለምናባዊው ዓለም ሱሰኛ እንዲሆኑ እያደረጋቸው ይገኛል።

ይህ የቴክኖሎጂ ሱሰኝነት በአእምሮ እድገት መዘግየት፣ በአካላዊ ጤና መታወክ፣ በማህበራዊ መስተጋብር ፍላጎት ማጣት እንዲሁም በእንቅልፍ እና በባህሪ መዛባት ላይ የጎላ ችግር እያስከተለ መሆኑን አስገንዝበዋል።

እነዚህን ችግሮች ለመከላከል ወላጆች ለልጆቻቸው ከስክሪን ነፃ የሆኑ የጋራ ጨዋታዎች እንዲሁም የንባብ ጊዜያትን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል።

ወላጆች የራሳቸውን የስክሪን አጠቃቀም በመገደብ ለልጆቻቸው አርአያ መሆን፤ ልጆች ቴክኖሎጂን የሚጠቀሙበትን የሰዓት ገደብና የይዘት አይነት መወሰን እንደሚገባቸው አጽንኦት ሰጥተዋል።

ችግሩን በዘላቂነት ለመቅረፍም መንግስት ተፈፃሚነት ያላቸውን የህግ ማዕቀፎች ማውጣት እንዳለበት አማካሪዋ ጠቁመዋል።

የሀገሪቱን እሴት እና ባህል የጠበቁ የዲጂታል ክህሎት ስልጠናዎችን ማዘጋጀትና የሳይበር ደህንነት መዋቅሮችን ማጠናከር፤ ስኬታማና ስነ-ልቦናው ጤናማ የሆነ ትውልድን ለማፍራት ወሳኝ መሆኑን አማካሪዋ ገልጸዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review