አዲስ አበባ ከተማ የመላው ኢትዮጵያውያን እንደ መሆኗ በ20ኛው የብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ላይ ለመታደም በከተማዋ የሚያልፉ እንግዶችን በህብረብሔራዊ አንድነት እና ወንድማማችነት መንፈስ እየተቀበለች እንደምትገኝ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር ገለጹ፡፡
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ላይ ለመታደም አዲስ አበባን በማቋረጥ ወደ ሆስዕና ከተማ እያቀኑ ለሚገኙ ዜጎች በከተማ አስተዳደሩ ደማቅ አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል፡፡
ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተነሱ እግዶች አዲስ አበባ በደረሱ ወቅት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት አፈጉባዔ ወይዘሮ ቡዜና አልከድር አቀባበል አድርገውላቸዋል።
የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ ምስክር ነጋሽ (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን በማጠናከር ሀገርን ለማልማት በጋራ መቆም ይገባቸዋል ብለዋል፡፡
20ኛው የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ህዝቦች በዓል ላይ ለመታደም አዲስ አበባን በማቋረጥ ወደ ሆሳዕና ከተማ እያቀኑ የሚገኙ ዜጎች በበኩላቸው፣ በተደረገላቸው አቀባበል ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
መዲናዋ ያከናወነቻቸው የልማት ስራዎችም አስደነናቂ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ከተማ አስተዳደሩ መዲናዋን አቋርጠው ለሚያልፉ እንግዶች የሚያደርገው አቀባበል የሚቀጥል መሆኑም ተመላክቷል፡፡
በሃብታሙ ሙለታ