ዘጠኝ የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ተዘጋጅተዋል

You are currently viewing ዘጠኝ የፌዴራል ልዩ አዳሪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር ተዘጋጅተዋል

AMN – ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም

በ2019 የትምህርት ዘመን ተማሪዎችን ተቀብለው ለማስተማር 9 የፌዴራል ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን የትምህርት ሚኒስቴር አማካሪ ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር ክንደያ ገብረሕይወት ገለጹ።

በትምህርት ሚኒስቴር የሚተዳደሩት እነዚህ ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ብቃት ያላቸው፣ ተወዳዳሪ የሆኑ፣ ሥነ-ምግባርን የተላበሱ እንዲሁም ለሀገር የሚበቁ የወደፊት መሪዎችን ለማፍራት የሚያግዙ ተቋማት መሆናቸውን ፕሮፌሰር ክንደያ አስገንዝበዋል።

ከመደበኛ ትምህርት ቤቶች በተለየ መልኩ በልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶቹ የተግባር እና የክህሎት ትምህርት ላይ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጥም ተገልጿል።

ይህም ተማሪዎች የተለያዩ ክህሎቶችን እንዲያዳብሩ፣ ቴክኖሎጂን በተግባር እንዲጠቀሙ እና ለወደፊት የሥራ እና የትምህርት ዓለም ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያግዛል።

በተጨማሪም፣ ከቻይና መንግሥት ጋር በተደረገው የትብብር ስምምነት መሠረት ከሚቀጥለው የትምህርት ዘመን ጀምሮ የቻይንኛ ቋንቋ በእነዚህ ትምህርት ቤቶች እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት እንደሚሰጥ ፕሮፌሰር ክንደያ ገልጸዋል።

በመሆኑም ወላጆች፣ መምህራን እና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ተማሪዎች ይህን አንደ ዋና የትምህርት እድል አድርገው እንዲጠቀሙበት የማበረታታት እና የማስተባበር ሥራ እንዲያከናውኑ ፕሮፌሰር ክንደያ ጥሪ አቅርበዋል።

የፌዴራል ልዩ አዳሪ ትምህርት ቤቶች በመላ ሀገሪቱ በስፋት እንዲዳረሱ ትምህርት ሚኒስቴር በሁሉም ክልሎች 13 ልዩ አዳሪ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶችን ለመገንባት በልዩ ትኩረት እየሰራ መሆኑም ከትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review