ስለ ዲስክ መንሸራተት ማወቅ ያለብዎት ወሳኝ መረጃ

AMN – ነሐሴ 12/2018 ዓ.ም

May be an image of one or more people and hospital

የጀርባ ጤንነት ለሰውነታችን አጠቃላይ እንቅስቃሴ፣ ጥንካሬ እና ጽኑ መዋቅር መሠረት ቢሆንም፣ በአኗኗር ዘይቤ ሳቢያ የሚከሰተው የዲስክ መንሸራተት ችግር ለብዙዎች ፈተና እየሆነ መጥቷል።

የአከርካሪ አጥንት 33 ከሚሆኑ አጥንቶች የተገነባ ሲሆን፤ በእነዚህ አጥንቶች መካከል የሚገኙ ትራስ መሰል ዲስኮች በአከርካሪ ላይ የሚደርሰውን ጫና የመቋቋም እና አጥንቶቹ እንዳይጎዱ የመጠበቅ ዋና ተግባር አላቸው።

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የነርቭ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ ግዛው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳስረዱት፤ የዲስኮች ውጫዊ አካል ጠንካራ ሽፋን ያለው ሲሆን የውስጠኛው ክፍል ደግሞ ክሬም መሰል ፈሳሽነት አለው።

የዲስኩ ጠንካራ ውጫዊ ሽፋን ሲቀደድ ወይም ሲላጥ፣ በውስጡ የሚገኘው ለስላሳ ፈሳሽ ወደ ውጭ በመውጣት ባልተገባ ቦታ ላይ ሲገኝ የዲስክ መንሸራተት ይከሰታል።

ዶ/ር ሲሳይ እንደሚሉት፣ ከ25 ዓመት ዕድሜ በኋላ በሚመጡ ተፈጥሯዊ ለውጦች ምክንያት የተወሰነ የዲስክ ማፈንገጥ ቢኖርም፣ በምርመራ ወቅት ማፈንገጡ የተገኘበት ግለሰብ ሁሉ ህመምተኛ ነው ማለት አይደለም።

ምንም ዓይነት ህመም ሳይሰማቸው ሙሉ ዕድሜያቸውን የሚኖሩ ሰዎች እንዳሉ ዶ/ር ሲሳይ ጠቁመው፣ ህመሙ የሚከሰተው የዲስኩ ማፈንገጥ ከነርቭ ማለፊያ ቀዳዳዎች መጣበብ ጋር ተያይዞ ነርቭ ላይ ጫና ሲፈጥር ብቻ ነው ብለዋል።

ችግሩ በታችኛው የጀርባ ክፍል ሲከሰት በመቀመጫ፣ በጭን፣ በባት እና በእግር መዳፍ ላይ ከፍተኛ ህመም የሚኖረው ሲሆን፤ በአንገት ክፍል ሲከሰት ደግሞ በትከሻና በእጅ ላይ ከፍተኛ ህመም ያስከትላል። ህመሙ ሳል ሲያስሉ፣ ሲያስነጥሱ ወይም ጀርባን ወደ የተወሰኑ አቅጣጫዎች ሲያንቀሳቅሱ በከፍተኛ ሁኔታ ይባባሳል።

ለዚህ ችግር ተጋላጭ ከሚያደርጉ ዋና ዋና ምክንያቶች መካከል የዕድሜ መግፋት አንዱ መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ሲሳይ ፣ በዚህም የተነሳ ዲስኮች ከዕድሜ ጋር ተያይዞ ተፈጥሯዊ ውሃማ ይዘታቸውን ስለሚያጡ የመለጠጥና የመቋቋም አቅማቸው ይቀንሳል ብለዋል።

ከመጠን ያለፈ የሰውነት ክብደት በአጥንትና በዲስኮች ላይ የማያቋርጥ ተጨማሪ ጫና ስለሚፈጥር፣ ጉልበት የሚጠይቁ ከባድ ሥራዎች፣ ተደጋጋሚ ከባድ ነገር ማንሳት፣ መጎተት፣ በድንገት ወደ ጎን መታጠፍና መጠማዘዝ እንዲሁም በዘር ችግሩ ሊከሰት ይችላል፡፡

ይህ ችግር ሲያጋጥም የአኗኗር ዘይቤን እና በዕለት ከዕለት አንቅስቃሴ አቀማመጥን ማስተካከል፣ የሰውነት ክብደት መቆጣጠር እና ማንኛውንም ክብደት ያለው ነገር ሲያነሱ የሰውነት አቋምን በትክክል መጠበቅ ወሳኝ መፍትሄዎች መሆናቸውን በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሊኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የነርቭ ሀኪም የሆኑት ዶ/ር ሲሳይ ግዛው ጠቅሰዋል።

በሐኪም ትእዛዝ የሚወሰዱ የህመም ማስታገሻዎችን መጠቀም፣ በመጀመሪያዎቹ ቀናት ቀዝቃዛ ነገር በቦታው ላይ በመያዝ እብጠትንና መቆጥቆጥን መቀነስ፣ ከጥቂት ቀናት በኋላ ደግሞ ሙቅ ነገር በመጠቀም ህመሙን ማስታገስ ይቻላል ብለዋል።

ከመጠን ያለፈ ረጅም እረፍት መገጣጠሚያዎች እንዲተሳሰሩና ጡንቻዎች እንዲደክሙ ስለሚያደርግ የፈውስ ሂደቱን ስለሚያወሳስበው፣ በምትኩ በሚመች አቅጣጫ አጭር ጊዜ አርፎ በመጠኑ መራመድ ተመራጭ እንደሆነ የህክምና ባለሙያው ይመክራሉ።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review