ኢትዮጵያ በተገበረችው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገት እንዲመዘገብ ማስቻሉን የገንዘብ ሚኒስትሩ አህመድ ሽዴ ገለጹ።
ሚኒስትር አህመድ ሽዴ እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ትግበራን አስመልክቶ በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ በኢትዮጵያ ይፋዊ የስራ ጉብኝት ያደረጉ ሲሆን፤ በዚህም የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን መመልከታቸው ተገልጿል።
ከጉብኝታቸው በተጨማሪ ከከፍተኛ የመንግስት ስራ ኃላፊዎችና ከግሉ ዘርፍ ተወካዮች ጋር ውይይት ማድረጋቸው ተመላክቷል።

የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ የተተገበረው የተሟላ የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም በሀገሪቱ ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት እንዲመዘገብ አስችሏል።
በብዝሃ የኢኮኖሚ እድገት ላይ የተመሰረተው ሪፎርም በሁሉም መስክ ከፍተኛ መነቃቃት መፍጠሩን አስታውቀዋል። የሪፎርም ትግበራው ጠንካራና ዘላቂ ልማት እንዲመዘገብ እንዲሁም ውጤታማ ስራዎች እንዲከናወኑ ማስቻሉን ተናግረዋል።
ሪፎርሙ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በሙሉ አቅም በመጠቀም፣ በስራ እድል ፈጠራና የዜጎችን የኑሮ ደረጃ በማሻሻል ረገድ ከፍተኛ ለውጥ ማስመዝገቡን ገልጸዋል። የዋጋ ግሽበትን በወሳኝ ደረጃ መቀነስ ማስቻሉን፣ የወጪ ንግድ እድገትና አጠቃላይ የንግድ ሁኔታው ከፍተኛ መሻሻል ማሳየቱን አስታውቀዋል።
ከሪፎርሙ በኋላ እየተመዘገበ ያለው ውጤት ኢትዮጵያን ከአፍሪካ ግዙፍ ኢኮኖሚ ባለቤቶች አንዷ እንዳደረጋትም ጠቁመዋል። የኢትዮጵያ የዕዳ ማሻሻያ ድርድር አዎንታዊ መሻሻል ለሪፎርም ስራዎች አስፈላጊ ጉዳይ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የመንግስት ገቢ እንዲያድግና በገበያ ላይ የተመሰረተ የተረጋጋ የውጪ ምንዛሬ እንዲኖር ማስቻሉንም ጠቅሰዋል። የዓለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅት የኢትዮጵያን የለውጥ አጀንዳ ለማራመድ ላደረገው አስፈላጊ ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።

በተለይ ጠንካራና ዘላቂ እድገት እንዲመዘገብ እና የእድገት ዘርፎችን በማስፋት በኩል ሪፎርሙ ከፍተኛ ውጤት ማስገኘቱን አስታውቀዋል።የግሉን ዘርፍ ውጤታማነትና በኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ሚና ከማሳደግ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን ጠቅሰዋል።
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናይጄል ክላርክ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ በኢትዮጵያ እየተተገበረ ያለው ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርም ስኬታማ እንዲሆን የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢኮኖሚውን የበለጠ ለማጠናከር በተዘረጋው የብድር ስርዓት በኩል ኢትዮጵያን ለመደገፍ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልፀዋል። የኢትዮጵያን ጠንካራ የኢኮኖሚ እድገት፣ የተሻሻለ የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትና ኢኮኖሚውን ገበያ-መር ለማድረግ እየተከናወነ ያለው ተግባር የሚበረታታ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ያስመዘገበችውን የኢኮኖሚ እድገት አድንቀው የተጀመሩትን የሪፎርም ስራዎች አጠናክሮ ማስቀጠል አስፈላጊ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡