የአንድ ጀምበር ፍሬዎች

You are currently viewing የአንድ ጀምበር ፍሬዎች


“የአንድ ጀምበር የስራ ዕድል ፈጠራው የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራን እንደሆነ ትልቅ ማሳያ ነው”

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ

ከጥገኝነት ለመላቀቅና ለሌሎች ወገኖች የስራ ዕድል ለመፍጠር እንደሚያግዛቸው የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችና ሴቶች ገልጸዋል

ወጣት እስማኤል ሀሺም በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 2 ነዋሪ ነው፡፡ ኑሮውን ለመምራት በታክሲ ረዳትነት፣ በሹፍርና እና ሌሎች የስራ መስኮች ሲሰራ እንደነበር ያነሳል። ነገር ግን ስራው ቀጣይነት የሌለው መሆኑና በራሱ ለመስራት በመፈለጉ ከጓደኞቹ ጋር በመሆን በወተት ከብት እርባታ ተደራጅተውና ስልጠና ወስደው የመስሪያ ቦታ እንዲሰጣቸው ሲጠባበቁ መቆየታቸውን ይናገራል፡፡

በአንድ ጀምበር የስራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄም፣ ወጣት እስማኤል እሱን ጨምሮ አምስት ሆነው ተደራጅተው ወደ ስራ ለመግባት የሚያስፈልጋቸውን 60 ካሬ ሜትር ስፋት ያለው የመስሪያ ቦታ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የ“እስማኤል፣ ሱለምና ጓደኞቻቸው የወተት ከብት እርባታ ህብረት ሽርክና ማህበር” ስራ አስኪያጅ የሆነው ወጣት እስማኤል፤ ስራ የሚጀምሩበት ሁኔታ ስለተፈጠረላቸው በጣም ደስተኛ መሆኑን ተናግሯል፡፡

“ስንጠብቀው የነበረ ዕድል ነው። የተደረገልን የመስሪያ ቦታ ድጋፍ ለስራችን ትልቅ ዋጋ ያለው ነው። በዚህ ዘርፍ የመስሪያ ቦታ ከሌለ ምንም መስራት አይቻልም፡፡” ሲልም ወደ ስራ እንዲገቡ ከተማ አስተዳደሩ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናውን አቅርቧል። እስማኤል በማብራሪያው፣ “በቀጣይም የሚያስፈልጋቸውን የብድር፣ የሙያና ሌሎች ድጋፎች እንደሚደረጉላቸው ቃል ተገብቶልናል፡፡ ወደፊትም በወተት ከብት እርባታ እና በወተት ማቀነባበር ላይ በሰፊው በመስራት ለበርካታ ወገኖች የስራ ዕድል የመፍጠር ህልም አለን” ብሏል፡፡

ሌላኛዋ የስራ ዕድል የተፈጠረላት ወጣት ትዕግስት ይመር ትባላለች። በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 ነዋሪ ናት፡፡ ትምህርቷን እስከ አስረኛ ክፍል ድረስ ተከታትላለች፡፡ በትምህርት ለመቀጠል ፍላጎት ቢኖራትም ውጤት ሊመጣላት ባለመቻሉ፤ ከቤተሰቦቿ ጋር ሆና መስተንግዶና ፅዳትን ጨምሮ የተገኘውን እየሰራች ነበር የምትኖረው፡፡ ከዚህ ባሻገር የስራ ዕድል እንዲፈጠርላት በምትኖርበት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 14 አስተዳደር በስራ ፈላጊነት ተመዝግባ መቆየቷን ትናገራለች፡፡

በአንድ ጀምበር የስራ ዕድል ፈጠራ ከሶስት ጓደኞቿ ጋር በመሆን በሻይና ቡና ንግድ ወይም “ቡና ጠጡ” በመደራጀት ስራ መጀመራቸውን አክላለች፡፡ የስራ ዕድል ስለተፈጠረላት ደስተኛ መሆኗን በመናገርም፣ ወደፊት ስራውን በማስፋት ለሌሎች ወገኖችም የስራ ዕድል የመፍጠር ህልም እንዳላቸው አክላለች፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በከተማዋ ለስራ ፈላጊ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል ለመፍጠር ልዩ ትኩረት በመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡ ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአንድ ጀምበር ለ30 ሺህ የከተማዋ ወጣቶችና ሴቶች የስራ ዕድል ተፈጥሯል፡፡ የስራ ዕድል የተፈጠረባቸው ዘርፎችም በአገልግሎት 13 ሺህ 637፣ በኮንስትራክሽን 7 ሺህ 781፣ በከተማ ግብርና 5 ሺህ 256፣ በማኑፋክቸሪንግ 2 ሺህ 359 እንዲሁም በንግድ 967 ዜጎች ናቸው፡፡

በአንድ ጀምበር የስራ ዕድል ፈጠራ መድረክ ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ እንደተናገሩት፣ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸውና ወደ ስራ የገቡት ቀደም ሲል የከተማ አስተዳደሩ ከነዋሪዎች ጋር ባካሄዳቸው የተለያዩ መድረኮች “የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው” ጥያቄ ሲያነሱ የነበሩ ወጣቶችና ሴቶች ናቸው። አስተዳደሩ በክህሎትና በእውቀት የበለፀገ፣ ጠንካራ ሞራልና ስነ ምግባር ያለው እንዲሁም ችግር ፈቺ የሆነ ትውልድ ለመፍጠር እየሰራ ይገኛል፡፡ በገበያው በሰለጠነ የሰው ሀይል ፍላጎትና አቅርቦት መካከል ያለውን ክፍተት ለመሙላትም በርካታ ወጣቶች አጫጭር ስልጠና እንዲወስዱ፣ የክህሎትና ሙያ ባለቤት እና በኢኮኖሚው ውስጥ ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡

“ትናንትና ስራ በመምረጥና ያለንን እምቅ አቅም በተሟላ ሁኔታ ባለመጠቀማችን የምንፈልገው የእድገት ደረጃ ላይ ሳንደርስ ቆይተናል፡፡” ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ነገ የተሻለ ይሆን ዘንድ የስራ ባህልን በማሳደግ፣ በፍጥነት እና በጥራት መስራትን መርህ በማድረግ እየተሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡

“ለ30 ሺህ ዜጎች በአንድ ጀምበር የስራ እድል መፍጠርና ስምሪት ማድረግ የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት እየሰራን እንደሆነ ትልቅ ማሳያ ነው” ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ በዕለቱ በከተማ ግብርና፣ ማኑፋክቸሪንግ፣ ኮንስትራክሽን፣ ንግድና አገልግሎት የስራ ዘርፎች ለስራ ፈላጊዎች የስራ ዕድል መፈጠሩን ተናግረዋል፡፡

“ወደ ስራ የገቡ ወጣቶችና ሴቶች ከፊታቸው የሚያጋጥማቸውን ፈተና ለማለፍ በርትተው መስራት ይገባቸዋል፤ የከተማ አስተዳደሩ ከጎናቸው በመሆን ድጋፍ ያደርጋል፡፡ በስፋት እየተተገበረ ያለው የአንድ ጀምበር የስራ ዕድል ፈጠራ ንቅናቄም በቀጣይነት በልዩ ትኩረት ተጠናክሮ ይቀጥላል” ሲሉም ከንቲባ አዳነች አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የስራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ በበኩላቸው፣ በመዲናዋ በ2018 በጀት ዓመት ለ350 ሺህ ዜጎች በቋሚነት የስራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ  እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን በአራት ወራት ጊዜ ውስጥ ለ158 ሺህ 138 ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል፡፡ ይህም በእቅድ ከተያዘው አኳያ 97 በመቶ ድርሻ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

ለዜጎቹ የስራ ዕድል የሚፈጠረው በተለያዩ አማራጮች ነው፡፡ ከቅጥር ባለፈ በተለያዩ ዘርፎች ስራ ፈላጊዎች እንዲደራጁ በማድረግ በአራት ወራት ውስጥ 40 ሺህ 71 አንቀሳቃሾች  ያላቸው 7 ሺህ 591 ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ወደ ስራ ማስገባት ተችሏል፡፡ ለኢንተርፕራይዞቹም የብድር፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታ፣ የማሽን አቅርቦትና የገበያ ትስስር ድጋፍ ተደርጎላቸዋል፡፡ በአንድ ጀምበር የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው 30 ሺህ ዜጎችም ውጤታማ እንዲሆኑ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግላቸው አቶ ሚሊዮን ተናግረዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኪሩቤል ሰለሞን ለዝግጅት ክፍላችን እንደተናገሩት፣ በአዲስ አበባ በአንድ ጀምበር ሰፊ የስራ እድል መፈጠሩ የከተማ አስተዳደሩና ከንቲባዋ ለወጣቶችና ሴቶች የሰጡትን ትኩረት ያሳያል፡፡ የወጣቶችን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ ከተማ አስተዳደሩ የጀመራቸው የአንድ ጀምበር የስራ ዕድል ፈጠራ ተነሳሽነት ይበል የሚያሰኝና ቀጣይነት ያላቸው ሊሆኑ ይገባል፡፡

እንደ ባለሙያው ገለጻ፣ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ወጣቶችና ሴቶች በስራቸው ውጤታማ እንዲሆኑ፣ ወደ ቀጣይ የእድገት ደረጃ እንዲሸጋገሩ፣ ወደ ባለሀብትነት አድገው ከራሳቸው ባለፈ ለሌሎችም ወገኖች የስራ እድል መፍጠር እንዲችሉ ተከታታይነት ያለው ድጋፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስራቸውን ሲያከናወኑ የሚገጥሟቸውን ችግሮች ማለፍ እንዲችሉ የቅርብ ድጋፍና ክትትል ማድረግ ይጠበቃል፡፡

አዲስ ወደ ስራ የሚገቡ ስራ ፈጣሪዎች (ኢንተርፕርነሮች) ወደ ስራው ዓለም ሲገቡ የቢዝነስ አመራር ችግር፣ የፋይናንስ እጥረት፣ በቁርጠኝነት አለመስራት፣ የገበያ ትስስርና መሰል ፈተናዎች ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉና እነዚህን ችግሮች ለማለፍ ከመንግስትና ከራሳቸው ከኢንተርፕርነሮች ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ አቶ ኪሩቤል አንስተዋል፡፡

ኢንተርፕራይዞች የማምረቻ ዋጋ በመቀነስ፣ ብዙ ምርት በጥራት በማቅረብ በገበያው ተወዳዳሪ ለመሆን መስራት ይጠበቅባቸዋል። መንግስት ኢንተርፕራይዞች ውጤታማ እንዲሆኑ በቅርብ ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል። በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ ለሆኑ ኢንተርፕራይዞች እውቅና እና ማበረታቻ መስጠት፣ በየእድገት ደረጃቸው ሊያገኙት የሚገባውን ድጋፍ ማቅረብና ሌሎች ደግሞ ከእነዚህ ተሞክሮ እንዲወስዱ በማድረግ መስራት እንደሚገባ አያይዘው ያነሳሉ፡፡

ከገበያ ትስስር ጋር በተያያዘ ኢንተርፕራይዞች በጥራት ማምረት ከቻሉ ገበያው ውስጥ መግባት ያን ያህል ሊያሳስባቸው እንደማይገባ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ተናግረዋል። ለምሳሌ፡- የኮንስትራክሽን ዘርፍ ላይ የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች በከተማዋ ካለው ሰፊና ፈጣን የግንባታ እንቅስቃሴ አኳያ ገበያ ማግኘት አይቸግራቸውም። በከተማ ግብርና ዘርፍም በዶሮ እርባታ፣ ወተት፣ የጓሮ አትክልት ልማትና ሌሎችም ስራዎች የሚሰማሩት በደንብ ማምረት ከቻሉ ገበያው ውስጥ መግባት ይችላሉ። በዋናነት በአነስተኛ የማምረቻ ዋጋ በማምረት ቀድሞው ገበያው ውስጥ ካሉት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን መትጋትና በርትተው መስራት ይኖርባቸዋል፡፡

የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ኪሩቤል እንደገለፁት፣ በከተማዋ የስራ ዕድል ፈጠራውን ለማሳደግ በርካታ የስራ ዕድል መፍጠር የሚችሉ የኢንዱስትሪ ዘርፎችን በመለየት ድጋፍና ማበረታቻ ማድረግ ይገባል፡፡ አዲስ አበባ ትልቅና ፈጣን እድገት እያስመዘገበች ያለች ከተማ ናት። የከተማ አስተዳደሩ በርካታ ተቋማት አሉት፤ ሰፊ መንግስታዊ አገልግሎትም ይሰጣል፡፡ ከዚህ አኳያ በከተማዋ ያለውን የስራ አጥነት ችግር ለመቅረፍ መረጃዎችን በመሰብሰብ፣ በመተንተንና ጥናቶችን በማካሄድ መፍትሔዎችን ማመላከት ይቻላል፡፡ ብዙ መቅጠር የሚችሉ ተቋማት ወይም ድርጅቶች እነማን ናቸው? ምን ድጋፍ ቢደረግላቸው አቅማቸውን ማሳደግ ይቻላል የሚለውን በመለየት መስራት ይገባል፡፡

በስንታየሁ ምትኩ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review