በሰላም ስምምነቱ መሰረት የተለያዮ ጉዳዮች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ከመንግስት ጋር ተስማምተናል- ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ

You are currently viewing በሰላም ስምምነቱ መሰረት የተለያዮ ጉዳዮች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ከመንግስት ጋር ተስማምተናል- ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ

AMN- ሕዳር 27/2018 ዓ.ም

በሰላም ስምምነቱ መሰረት የተለያዮ ጉዳዮች ተፈፃሚ እንዲሆኑ ከአማራ ክልል መንግስት ጋር ተስማምተናል ሲሉ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ተናገሩ።

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት እና በአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት መካከል ዘላቂ የሰላም ስምምነት ማድረጋቸውን ተከትሎ የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የውጭ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊ ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ፤ በነበረው ግጭት እንደ ሀገርና እንደ ክልል ዋጋ አስከፍሎናል ያሉ ሲሆን መሰረተ ልማቶች እንዳይሰሩና ልማቶች እንዳይካሄዱ አድርጎ ቆይቷል ብለዋል።

በመሆኑም የሰላም ስምምነቱን ተከትሎ ከስምምነቱ በኃላ ተፈፃሚ የሚሆኑ ነጥቦችን አንስተዋል።

በዚህም መሰረት፦ የዜጎችን ደህንነት ማስጠበቅና የተፈናቀሉ ዜጎችን እንዲያስመልስ፣ የእኩል ተጠቃሚነት በክልሎች መካከል እንዲኖር ማስቻልና በዚህም አማራ ክልልን እንደሌሎች ክልሎች እንዲለማ ማድረግ፤ በፋኖ ስም የታሰረና የገንጣይ አስገንጣይ ተግባር የሌላቸው እንዲፈቱ፤ በግጭቱ የተጎዱ እንዲረዱ ማድረግ፣ በፋኖ ውስጥ ያሉ በመንግስት ስራ ላይ የነበሩ እውቀትና አቅም ያላቸው ዜጎች ወደ ስራ እንዲመለሱና ጥቅማቸው እንዲከበሩ ማድረግ ላይ ስምምነት መደረሱን ካፒቴን ማስረሻ ገልፀዋል።

በተጨማሪም በፋኖ አደረጃጀት ያሉ ታጣቂዎች በመደበኛ ሰራዊት አደረጃጀት ታቅፈው ወደ መደበኛ ሰራዊት አባልነት እንዲካተቱና ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ስምምነት መደረሱን አብራርተዋል።

ትግሉ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ፍላጎታቸውን ለማሟላት ያቀዱበት እንደነበር በመግለፅ፤ ይህንንም በመረዳት ሌሎች ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ ሀይሎች ይህንን በመረዳት ወደ ሰላም ስምምነት እንዲመጡ አሳስበዋል።

የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅት የመረጃ ደህንነት መመሪያ ኃላፊ እና የኮር ስራ አስፈጻሚ መስፍን አባተ በበኩላቸው፤ እንደ ሀገርና እንደ ክልል ሰላምን ለማስጠበቅ የምስራቅ አፍሪካን አሰላለፍን መረዳትና የሀገርን ጥቅም ማስከበር ይገባል ብለዋል።

በዚህም የኢትዮጵያን ጥቅም በጋራ ማስከበር ይገባል ሲሉ ገልፀዋል። ስምምነቱን የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አረጋ ከበደ እና የአማራ ፋኖ ህዝባዊ ድርጅትን በመወከል ካፒቴን ማስረሻ ሰጤ ሰሞኑን መፈረማቸው ይታወሳል።

በንጉሱ በቃሉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review