እልባት ያጣዉ የመካከለኛዉ ምስራቅ ግጭት እና በጉጉት የሚጠበቀዉ ሁለተኛዉ የአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ንግግር

You are currently viewing እልባት ያጣዉ የመካከለኛዉ ምስራቅ ግጭት እና በጉጉት የሚጠበቀዉ ሁለተኛዉ የአሜሪካ እና ኢራን የሰላም ንግግር

AMN ሚያዝያ 17/2018 ዓ.ም

በመካከለኛዉ ምስራቅ የተከሰተዉ ግጭት ጦርነት ዉስጥ ለገቡትና ዳፋዉ ለደረሳቸዉ አገራት ብቻ ሳይሆን ለተቀረዉ ዓለም ጭምር ግራ አጋቢ ክስተት ሆኖ ቀጥሏል፡፡

አብዛኛዉ የዓለም ህዝብ በአሜሪካ፤ እስራኤልና ኢራን መካከል የተከሰተዉ ግጭት መች እልባት ያገኝ ይሆን ብሎ በጉጉት በመጠበቅ ላይ ይገኛል፡፡

ጦርነቱ በርካታ ንጹህን ዜጎችን ለሕልፈት ዳርጓል፣ በርካቶች ከሰላማዊ በኑሮአቸዉ እንዲፈናቀሉ፣ መሰረተ ልማቶች እንዲወድሙ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች እንዲስተጓጎሉም ምክንያት ሆኗል፡፡

ከሁሉም በላይ ከዓለም አቀፉ የነዳጅ ጭነት አንድ አምስተኛዉ የሚተላለፍባት የሆርሙዝ የባህር ወሽመጥ በጦርነቱ ምክንያት ከፍተኛ እሰጣ ገባ ዉስጥ መግባቷ የኃይል ዋጋ ላለፉት በርካታ ዓመታት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል፡፡

የዋጋ ግሽበትን አባብሷል፣ የዓለም አቀፍ የኢኮኖሚ እድገት ተስፋን አጨልሟል፣ የተቀረዉን ዓለም የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ ትልቅ ፈተና ዉስጥ ከቷል፡፡

አሜሪካ የኢራን የነዳጅ ምርት ወደ ውጭ እንዳይላክ እገዳ መጣሏ ደግሞ ክስተቱን ይበልጥ አሳሳቢ ማድረጉን ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙሃን ትኩረት ሰጥተዉ እየዘገቡት ይገኛሉ፡፡

ዘጠነኛ ሳምንቱን የያዘው የመካከለኛዉ ምስራቅ ግጭት መጨረሻዉ ምን ይሆን የሚለዉ ጥያቄ ለጊዜዉ ማንም ሊመልሰዉ ያልቻለዉ ጥያቄ ቢሆንም እንደወትሮው ሁሉ አሜሪካንን እና ኢራንን ለማቀራረብ ጥረት በማድረግ ላይ የምትገኘዉ ፓኪስታን ዛሬም ሁለቱን አገራት ዳግም ለማሸማገል በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡

የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ለዚሁ ጉዳይ ፓኪስታን መግባታቸዉንም ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

ሁለተኛውን የአሜሪካ-ኢራን የሰላም ንግግር ለማስተናገድ በዝግጅት ላይ ባለችው ኢስላማባድ ውስጥ ዋና ዋና መንገዶች ተዘግተው እና የህዝብ ትራንስፖርት ተቋርጦ ጥብቅ የደህንነት ጥበቃ እየተደረገ ይገኛል፡፡

ዋይት ሃውስ ጦርነቱን በሰላም ለመቋጨት ከመጋረጃ ጀርባ ከፍተኛ ጥረት እያደረገች እንደምትገኝ የተነገረ ሲሆን የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እስማኤል በቀኢ በበኩላቸዉ በሁለቱ አገራት መካከል ቀጥተኛ ስብሰባ የማድረግ እቅድ እንደሌለ አስታውቀዋል።

ሆኖም ንግግሩ መቀጠሉ በሁለቱም ወገኖች መካከል ለስምምነት ፍላጎት መኖሩን ያመላከተ ሲሆን አሜሪካ ስምምነቱ ትርጉም ባለው መንገድ ሊረጋገጥ የሚችለዉ ኢራናዊያን የኑክሌር ፍላጎታቸውን መተው ሲችሉ ብቻ ነው ማለቷም ተነግሯል፡፡

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አርብ ዕለት ለሮይተርስ እንደተናገሩት፣ ዋሽንግተን ከማን ጋር እየተደራደረች እንደሆነ ለመግለጽ ፈቃደኛ ባይሆኑም “አሁን በስልጣን ላይ ካሉት ሰዎች ጋር እየተገናኘን ነው” ብለዋል።

የዋይት ሃውስ የፕሬስ ፀሐፊ ካሮላይን ሌቪት በበኩላቸው፣ ባለፉት ጥቂት ቀናት በኢራን በኩል የተወሰነ መሻሻል መታየቱን እና በዚህ ቅዳሜና እሁድ ተጨማሪ ውጤት እንደሚጠበቅ ገልጸዋል።

በተጨማሪም ምክትል ፕሬዝዳንት ጄዲ ቫንስ ወደ ፓኪስታን ለመጓዝ ዝግጁ መሆናቸው ተነግሯል።

ሁለቱ ወገኖች ከስምምነት ላይ መድረሳቸዉ በነዳጅ አቅርቦትና ዋጋ መናር እየተፈተነ ለሚገኘዉ ለተቀረዉ ዓለም ትልቅ መፍትሄ ይሆናል ተብሎ በብዙሃኑ ዘንድ እየተጠበቀ ነዉ፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review