AMN – ሚያዝያ 18/2018 ዓ.ም
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ቅጠል ተራ አካባቢ የተጀመረውን የቤት ግንባታ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለነዋሪዎች ለማስረከብ እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር አያልነሽ ሀብተማርያም ተናገሩ፡፡
የቢሮ ሃላፊዋ በመርካቶ ቅጠል ተራ የቤት ግንባታ ማስጀመሪያ ላይ ባደረጉት ንግግር ÷በከተማዋ የነዋሪዎችን የቤት ችግር ለመፍታት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆኑም አንስተዋል፡፡
በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ የሚሰራው ባለ 8 ወለል ግንባታ ፣ ለስራ እድል ፈጠራ የሚሆኑ ሱቆችንና በሺህዎች የሚቆጠሩ መኖሪያ ቤቶችን ያካተተ መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

ይሄ በአዲስ አበባ ከተማ ስማርት ሲቲን ከመመስረት አኳያ ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረውም ጠቁመዋል፡፡
የተጀመረውን የቤት ግንባታ በአጭር ጊዜ አጠናቆ ለነዋሪዎች ለማስረከብ እንደሚሰራ በማንሳት ግንባታውን ለማጠናቀቅ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
የቤት ግንባታ የተጀመረበት አካባቢ ለኑሮ አስቸጋሪ እንደነበር ያስታወሱት ደግሞ የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ ታረቀኝ ወርቅነህ ናቸው፡፡
የተጀመረው ግንባታ የነዋሪዎችን የቆየ ችግር እንደሚፈታ በማንሳት አሁን ላይ ለኑሮ ምቹ ወደሆነ አካባቢ እንዲቀየር አቅጣጫ ተቀምጦ የመሰረተ ድንጋይ መጣሉን አንስተዋል፡፡
ገንባታውን አጠናቆ ለነዋሪዎች በፍጥነት ለማስረከብ የድጋፍና የክትትል ስራዎች ይሰራሉ ያሉት ዋና ስራ አስፈጻሚው ግንባታው ሲጠናቀቅ የዜጎችን የአኗኗር ዘይቤ እንደሚቀይርም አመላክተዋል፡፡
የሻምበል ምሕረት