ብልጽግና ፓርቲ ለ20ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች ቀን በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።
ፓርቲው ያስተላለፈው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለ20ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል አደረሰን አደረሳችሁ!
የ2018 ዓ.ም የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል በየደረጃውና በተለያዩ ኩነቶች ሲከበር ቆይቶ በዛሬው ቀን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ በደማቅ የማጠቃለያ መርሀግብር እየተገባደደ ይገኛል፡፡
የዘንድሮው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ከህዳር 01 ጀምሮ ለተከታታይ አንድ ወር በሁሉም ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በደማቅ ኩነት እንዲከበር ተደርጓል፡፡ ይህም እውነተኛ ህብረብሄራዊ አንድነት እና ፌዴራላዊ ሥርዓት ለመገንባት የተያዘው ቁርጠኝነት ማሳያ ነው፡፡
ብልፅግና ፓርቲና የመደመር መንግሥት 20ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ከዕለታዊ ክብረበዓል በላይ የአጀንዳው ትክክለኛ አስፈላጊነት በውል በመረዳት በበዓሉ ስያሜ የተገለጹትን የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች የፍትህ፣ የእኩልነት፣ የልማትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎች በተግባር በመመለስ መሆን አለበት ብሎ ያምናል፡፡ ለዚህም በዓሉ በአንድ ቀን ከማክበር አንድ ወር ሙሉ በመውሰድ በየክልሉና ከተማ አስተዳደሩ ያሉት ባህሎችና ነባራዊ እውነታዎች ታሳቢ በማድረግ በተከታታይ እንዲከበር መደረጉ የዚህ እምነት አንዱ ማሳያ ነው፡፡
በዓሉ “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረብሄራዊ አንድነት” በሚል መሪ ቃል እንዲከበር የተመረጠበት ምክንያት እውነተኛ ህብረብሄራዊ አንድነት እና ፌዴራላዊ ሥርዓት የሚገነባው ዴሞክራሲያዊ መግባባት በመፍጠር መሆኑ በግልጽ አመላክቷል፡፡ ዴሞክራሲያዊ መግባባት ወይም የመግባባት ዴሞክራሲ የሀገራዊ ለውጡ ትሩፋት ከሆኑ ዕሳቤዎችና ተግባራት አንዱ ሲሆን የሀገራችን የዘመናት ችግር እና የሥርዓት ስብራት ሆኖ የቆየውን የዴሞክራሲ ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ እየተተገበረ ያለ ዕሳቤ ነው፡፡
ዋነኛው የኢትዮጵያ የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥያቄ የዴሞክራሲ ጥያቄ ነበረ፡፡ ከለውጡ በፊት በነበሩት ዓመታት ይህንን በዓል የዕሳቤ ጥራት እና የተግባር ቁርጠኝነት ያልተፈጠረበት የይስሙላ የአደባባይ ትዕይንት ሆኖ ሲከበር ቆይቷል፡፡ ሙሉ ዕይታን መለያው ያደረገው ብልፅግና ፓርቲ ይህንን የዕይታና የተግባር ክፍተት በማረቅ የጎደሉትን የእውነተኛ ህብረብሄራዊ አንድነት፣ ፌዴራላዊ ሥርዓት እና ዴሞክራሲያዊ መግባባት አላባውያን በማገናኘት ወደ ተቃና የለወጥና የዝላይ ምዕራፍ እንዲገባ አድርጎታል፡፡
ዴሞክራሲያዊ መግባባት የተዋንያን በተለይ ደግሞ የህዝብ ይሁንታና ተሳትፎ የሚያስተናግድ ዕሳቤና ማህበራዊ ውል ነው፡፡ የዴሞክራሲያዊ መግባባት አንዱና ዋነኛ መገለጫ ምርጫ ሲሆን የዘንድሮው የህዳር 29 በዓል ከ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው፡፡ ያለፈው 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ ለዴሞክራሲያዊ መግባባት መሠረት የጣለ ስኬታማ ምርጫ እንደነበረው ዘንድሮ የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ደግሞ የዚህ ዕሳቤና ማህበራዊ ውል የአፈጻጸም ከፍታ የሚታይበት እንዲሆን አስፈላጊውን ዝግጅት ሁሉ እየተጠናቀቀ ይገኛል፡፡
በዓሉ በያዝነው ዓመት ሲከበር የኢትዮጵያ ብልፅግና አይቀሬ ሀገራዊና ዓለምአቀፋዊ ፕሮጀክት መሆኑ በአያሌ ማሳያዎች የተረጋገጠበት በመሆኑ በዓሉ ይበልጥ ደማቅ አድርጎታል፡፡ የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ መመረቅ ብልፅግና ፓርቲ ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር እንደሚፈጸም ማሳያ ነው፡፡ በዕለቱ የተበሰሩ 7ቱ በጉባ ብስራቶች የመደመር መንግሥት ትሩፋቶች ሆነው የዚህ ተግባር ቀጣይነት በማሳየት በህዝብ ዘንድ ከፍተኛ መተማመንና ቅቡልነት ለመፍጠር ተችሎበታል፡፡
ይህ በመፍጠን፣ መፍጠርና ዝላይ የታጀበ አስደናቂ የልማት አርበኝነት የባህር በር አጀንዳችን ላይ ለመድገም ስንቅ በመሆን “ከግድቡ ወደ ባህሩ” በሚል ህዝባዊ መፈክር ከታሪካችንና ከማንነታችን አለአግባብ የተወሰደብንን የባህር በር ጥያቄያችን በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ለማስመለስ እንደ ህዝብና ሀገር አንድ ሆነን እየሰራንበት እንገኛለን፡፡
20ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል ስናከብር የመደመር መንግሥት ያስቀመጣቸውን አሻጋሪና ተስተካካይ ዕቅዶች እየተተገበሩና ውጤት እያመጡ መሆናቸውና ለዚህም ህዝብ በባለቤትነት የሚሳተፍበትና ተጠቃሚ እየሆነበት ያለ መሆኑ በመገንዘብ ነው፡፡
በቀጣይ ዓመት 21ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል የምናከብረውም በአንድ እጃችን የጀመርናቸው የፀጥታና የልማት ሥራዎች አሳክተን በሌላው እጃችን ደግሞ ህዝቦች ለዘመናት የታገሉለትን የዴሞክራሲ ሥርአት ወደ ላቀ ደረጃ አድርሰን ነው፡፡
በጉጉት የሚጠበቀውና ነጻ፣ ፍትሀዊና አሳታፊ በመሆን የዴሞክራሲ እመርታ እንዲፈጠርበት በሚጠበቀው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንደ ከዚህ ቀደሙ በባለቤትነትና በላቀ ተነሳሽነት በመሳተፍ መሆን አለበት፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የሀገራችን ፀጥታ፣ ልማትና ዴሞክራሲ የሚጎመዝዛቸው ባዳዎችና ባንዳዎች ሀገር አፍራሽ እንቅስቃሴዎቻቸውን በንቃት በመከታተልና በመመከት እንዲሁም በዛሬው ቀን በድምቀት እያጠቃለልነው ያለነው በዓል መሪ ቃል የሆነውን “ዴሞክራሲያዊ መግባባት ለህብረብሄራዊ አንድነት” ተግባራዊ ለማድረግ ዴሞክራሲያዊ መግባባታችንን እና ህብረብሄራዊ አንድነታችንን በማጽናት መሆን አለበት፡፡
መልካም 20ኛው የኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓል!
ብልፅግና ፓርቲ
ህዳር 29፤ 2018 ዓ.ም