በጥራታቸው የሚታወቁት የደቡብ ኮሪያ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ወደ ሥራ እንዲገቡ መንግሥት አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆኑን አምባሳደር ደዋኖ ከድር ገልጸዋል።

የኮሪያ ስፔሻሊቲ ተቋራጮች ማኀበር፣ በኢትዮጵያ የግንባታው ዘርፍ ለመሠማራት ያሳየው ፍላጎት የሚበረታታ እንደሆነም አንስተዋል።

የሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ ትብብር የሀገራቱን ቀጣይነት ያለው ተጠቃሚነት ለማሳደግ የሚያግዝ መሆኑን የጠቀሱት ዓይናለም አባይነህ (ዶ/ር)፣ ምክር ቤቱም የውጭ ኩባንያዎችን ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር በማስተሳሰር እንዲሁም በግሉ ዘርፍ እና በመንግሥት መካከል አገናኝ ድልድይ በመሆን እንደሚሠራ ገልጸዋል።

በሁለቱ ሀገራት የረጅም ጊዜ የኢንቨስትመንት አጋርነትን ለማጠናከር በአይሲቲ፣ በማምረቻ መስኮች፣ በግንባታ፣ በኃይል አቅርቦት እና በሌሎች መሰል ዘርፎች መሠማራት እንደሚችሉ እና ለዚህም ምቹ የኢንቨስትመንት ከባቢ እንደሚፈጥር በፎረሙ ላይ ተጠቁሟል።

በፎረሙ ከኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የመካከለኛው ምስራቅ፣ እስያ እና ፓስፊክ ሀገራት ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ደዋኖ ከድር፣ በኢትዮጵያ የደቡብ ኮሪያ አምባሳደር ካንግ ጁንግ፣ የኢትዮጵያ የንግድና ዘርፍ ማኀበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር አይናለም ዓባይነህ፣ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዳጋቶ ኩምቤ፣ የኮሪያ ስፔሻሊቲ ተቋራጮች ማኀበር ኃላፊዎች እና የሁለቱ ሀገራት የቢዝነስ ተቋማት ተወካዮች ተገኝተዋል።
በአይናለም አባይነህ