ኢትዮጵያ ባለፉት የለውጥ ዓመታት ላስመዘገበችው ስኬት ባለ ራእይ፣ ሀገር ወዳድ መሪን እና ስራዎችን ከህዝብ ጋራ እየመከረ የሚሰራ መንግስት በማግኘቷ ነው ሲሉ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ተናገሩ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጌዲኦ ዞን ዲላ ከተማ “የጉባ ብስራቶች የመደመር መንግስት ትሩፋቶች” በሚል መሪ ሀሳብ ህዝባዊ ውይይት እየተካሄደ መሆኑ ተገልጿል።
በመድረኩ የተገኙት የትራንፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትር አለሙ ስሜ (ዶ/ር) ባለፉት ሰባት ዓመታት የዜጎችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ እና የሀገርን ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚያረጋግጡ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ለተመዘገቡ ስኬቶች መንስኤው ሀገሪቷ ባለራእይ እና ሀገር ወዳድ መሪ በማግኘቷ እና መንግስትም የሚሰራቸውን ስራዎች ከህዝቡ ጋር እየመከረና እየተቀናጀ በመከወኑ ትልቅ ስኬት መመዝገቡን አንስተዋል።
ውይይቱ ስኬት የተመዘገበባቸው ስራዎችን ለመገምገም እና በቀጣይ መከናወን ለሚገባቸው ስራዎች የጋራ ተልእኮ ለመውሰድ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
ከዚህ ባለፈም መንግስት የህዝቡን የመደመጥ መብት ከቃል ባሻገር በተግባር ለማክበር እና ባለፉት የውይይት መድረኮች የተነሱ ችግሮች መፍትሄ የተሰጣቸውን እና ቀሪ ስራዎችን ለመገምገም ያለመ መድረክ ስለመሆኑም ገልጸዋል።
የተሳኩ ትልሞችን በማጽናት ወደ ፊት ለሚከናወኑ ስራዎች የህዝቡን ስሜት በማድመጥ የጋራ ተልእኮ መውሰድ የመድረኩ ዋና አላማ መሆኑን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በሔኖክ ዘነበ