“ከተወለድኩ ጀምሮ ምላጭ በፀጉሬ ላይ አርፎ አያውቅም” – ወይዘሮ ገነት ከበደ ረጋሳ

You are currently viewing “ከተወለድኩ ጀምሮ ምላጭ በፀጉሬ ላይ አርፎ አያውቅም” – ወይዘሮ ገነት ከበደ ረጋሳ

AMN- ታኅሣሥ 9/2018 ዓ.ም

ወይዘሮ ገነት ከበደ ረጋሳ ትባላለች። የፀጉሯ ርዝመት 1 ሜትር ከ50 ሴንቲ ሜትር ይደርሳል። ፀጉሯ በጀርባዋ ላይ የሚያርፍ ብቻ ሳይሆን እስከ ጉልበቷ ድረስ የሚረዝም ነው።

ስለ ፀጉሯ ርዝመት ስትናገርም “ፀጉሬን ለመንከባከብ የሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ከባለቤቴ እጅ አይጠፋም” ስትል ለኤ ኤም ኤን ዲጂታል ተናግራለች።

በምዕራብ ሸዋ ዞን በጅባት ወረዳ ኩዩ አሬሬ ቀበሌ ተወልዳ እንዳደገች የምትናገረው ገነት፣ በአሁኑ ወቅት በዚሁ ዞን በኖኖ ወረዳ የመሬት አስተዳደር ቢሮ ሰራተኛ ናት።

“ፀጉር ለሴቶች የውበት መገለጫ ነው፤ በጣም ስለምወደውም ሳልታጠብ አንድ ሳምንት ካለፈኝ ደስ አይለኝም” ትላለች።

“እኔና ፀጉሬ እድሜያችን እኩል ነው፤ 30 አመታት ሆኖናል” የምትለዉ ገነት ጸጉሯን ምላጭ ነክቶት እንደማያውቅና ገና ስትወለድ በነበረው ሁኔታ ላይ እንዳለ ገልጻለች።

ከአቮካዶ የሚዘጋጁ የቅባት አይነቶችን እንደምትጠቀምና እንደምትከባከብ በመጥቀስ፣ ፀጉሯን ለቃው እንደማትሄድና ጠቅልላ እንደምትይዘው ተናግራለች።

ገነት የሁለት ልጆች እናት መሆኗን አንስታ “ለልጆቼም እኔ የምጠቀመውን ቅባት እቀባቸዋለሁ” ስትል የልጆቿም ፀጉር ረጅም መሆኑን ተናግራለች።

በቤተሰቦቿ ውስጥ እንዲህ ያለ ረጅም ፀጉር ያለው ባይኖርም፣ ሁለት እህቶቿ ጥሩ ፀጉር እንዳላቸውም ገልጻለች።

ፀጉሯን ለቃው በሰው ፊት ሄዳ እንደማታውቅ ገልጻ፣ “አንድ ቀን ግን በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ለቅቄው ስሄድ ሰዎች በግርምት ወደ እኔ ሲመጡና ሲጮሁብኝ በፍጥነት ሰብስቤ አሰርኩት” ብላለች።

“ሰው ፀጉሩን ለቆ ተውቦ ሲሄድ እመኛለሁ፤ እኔ ግን ለቅቄው በሰው መካከል ሆነ ወደ ስራ ቦታ ለመሄድ አልችልም” በማለት አስረድታለች።

ፀጉሯን ስትታጠብ ብቻዋን ስለማትችል ባለቤቷ እንደሚረዳት በመግለጽ፣ በዚህ አጋጣሚ ምስጋናዋን አቅርባለች።

ወጣቶችም ሰው ሰራሽ ፀጉር (ዊግ) በመጠቀም ገንዘባቸውን ከመጨረስ ይልቅ የራሳቸውን ፀጉር በመንከባከብና ፀጉራቸው የሚወደውን ትክክለኛ ቅባት መቀባትና መጠበቅ እንዳለባቸው ተናግራለች።

ከዚህም በተጨማሪ ፀጉር በሚቀባበት መንገድ መቀባት፤ በሚፈለገው ሰዓት በመታጠብና በመንከባከብ ፀጉርን ውብ እንደሚያደርግና እንደሚያሳድግ ከራሷ ተሞክሮ በመነሳት አብራርታለች።

ፀጉር ፈጣሪ ገና የሰዉ ልጅ ሲፈጠር የሚሰጠው ስጦታ ቢሆንም፣ ሴቶች ጸጉራቸዉን መንከባከብ እንዳለባቸው መልእክቷን አስተላልፋለች።

ወይዘሮ ገነት “ይህን ፈጣሪ የሰጠኝን ስጦታ እንደሌሎች ሴቶች ባጌጥበት እና ባሳየው ምኞቴ ነው” በማለት ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራት ቆይታ ተናግራለች።

በደራርቱ ተሬሳ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review