AMN- ሰኔ 22/2018 ዓ.ም
በቬንዙዌላ በተከሰተው የመሬት መንቀጥቀጥ ከቤት ፍርስራሽ ውስጥ ከ18 ቀናት ጨቅላ ልጇ ጋር በሕይወት የተረፈችው እናት መነጋገሪያ ሆናለች፡፡
ዳያና ፓቲኖ የተባለችው እናት፣ ልጄ በሕይወት እስካለ ድረስ እኔም በሕይወት መቆየት እችላለሁ በሚል ጽናት በፍርስራሹ ውስጥ ለሰዓታት መቆየቷን ተናግራለች፡፡
ልጇ ሁዋን ዳቪድን መተንፈሱንና በሕይወት መኖሩን ለማረጋገጥ በተደጋጋሚ አፍንጫውን ስትዳስስ እንደነበረ የተናገረችው ዳያና ፓቲኖ፣ ከፎቅ ፍርስራሽ በታች ያሳለፈቻቸው ሰዓታት አስፈሪ እንደነበሩና ትንሹን ልጇን አቅፋ ለመዳን ትጸልይ እንደነበር ገልጻለች።
ዳያና ፓቲኖ፣ የመሬት መንቀጥቀጡ ሲከሰት በሰሜናዊ የባህር ዳርቻ ላ ጉዋይራ በሚገኘው ባለ ስምንት ፎቅ አፓርታማዋ ውስጥ ዕቃ እያጠበች ነበር።
በዚህ መሃል ቀላል ንዝረት ሲሰማት ወዲያውኑ ልጇን ለማቀፍ ሮጠች፡፡

በወቅቱ ከቤት ዕቃዎች ጋር ተጋጭቼ ነበር፤ ልጄን እንዴት እንዳልለቀቅኩት አላውቅም ስትል ተናግራለች፡፡
ወዲያውኑ መጮህ ጀመርኩ፤ ነገር ግን ማንም ሊሰማኝ እንደማይችል በመረዳቴ ዝምታን መረጥኩ፡፡
ጉልበቴን በከንቱ አልጨርስም፤ የሰዎችን ድምጽ ወይም የእግር ኮቴ በአቅራቢያዬ ስሰማ እጮኻለሁ ብዬ ወሰንኩ ትላለች፡፡
ግራ እግሬን ኮንክሪት ስለተጫነው መንቀሳቀስ ባልችልም፣ ግንባሬንም አለት ተጭኖት ነበር ያለችው እናት፣ ያንን ያህል ሰዓታት እንዴት ተረጋግቼ መቆየት እንደቻልኩ አላውቅም ስትል አክላለች።
ዳያና ከስሯ መጽሐፍ ቅዱስ እንዳለ ስታውቅ ተስፋ እንዳገኘች ተናግራለች፤ የህልውና ጉዞዬ ከዚያ ተጀመረ ብላለች።
በፍርስራሹ ጨለማ ውስጥ እንደ ጨረቃ የምታበራ ጥንቅቅ ያለች የብርሃን ነጥብ ማየት ትችል እንደነበር ያነሳችው ዳያና፣ ወንድሟ ስሟን ሲጠራ ከሰማች በኋላ የመዳን ተስፋዋ በእጅጉ መለምለሙን ተናግራለች።

ይህ የእኔ ብቸኛው ዕድል ነው አልኩኝ፤ ያለኝን ኃይል በሙሉ ተጠቅሜ ጮህኩኝ… ‘እዚህ ነኝ’ ብዬ ጮህኩ፤ ወንድሜም ‘አግኝቼሻለሁ፣ እስካወጣሽ ድረስ ጥዬሽ እንደማልሄድ ቃል እገባልሻለሁ’ አለኝ ስትል በወቅቱ የገጠማትን ፈታኝ ቆይታ አስረድታለች፡፡
ከዚያ በኋላም የነፍስ አድን ሰራተኞች ባደረጉት ብርቱ ጥረት እናቲቱንና ህጻኑን ከፍርስራሹ ውስጥ በጥንቃቄ አውጥተዋል፡፡
በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ዳያና በሁለቱም እግሮቿ ላይ ጉዳት የደረሰባት ሲሆን፣ ሁዋን ግን እድለኛ ሆኖ ቀላል ጉዳት ብቻ አስተናግዷል።
ከቤት ፍርስራሹ ውስጥ በጤንነት የወጣው ልጇ ሁዋን ዳቪድ፣ ቢያንስ 1 ሺህ 450 ሰዎችን ለህልፈት በዳረገው የመሬት መንቀጥቀጥ በከፍተኛ ሁኔታ ለተጎዳችው ቬንዙዌላ የተስፋ ምልክት ሆኗል።

የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት በቬንዙዌላ ታሪክ “በጣም አስከፊው የተፈጥሮ አደጋ” ሲሉ የገለጹት ሲሆን፣ በዚህ ክስተት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም የደረሱበት አልታወቀም።
የፍለጋ ሥራው ተጠናክሮ የቀጠለ ቢሆንም፣ በሕይወት የተረፉ ሰዎችን የማግኘት ተስፋ ግን እየመነመነ መምጣቱን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ