የትውልድ ድምፅነት በየፈርጁ

You are currently viewing የትውልድ ድምፅነት በየፈርጁ

ኤ ኤም ኤንን ጨምሮ 12 ተቋማት የፈጠሩት ጥምረት ሚዲያው የትውልድ ድምፅነቱን አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚያግዘው ተገልጿል

ዘመናዊ ቴክኖሎጅን ከብቁ የሰዉ ኃይል ጋር አቀናጅቶና በመዲናዋ የሚታዩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት መፍትሔ እንዲሰጥና የአዲስ አበባ ከተማን ገጽታ ለዓለም ጎልቶ እንዲታይ፣ በመንግስት እና በሕዝብ መካከል ያለው መስተጋብር የሰመረ እንዲሆን በማድረግ ረገድ ከከተማዋ እድገት ጋር አብሮ ከፍ እያለ የመጣው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በሕትመት እንዲሁም በዲጂታል አማራጮች መረጃዎችን ተደራሽ እያደረገ ይገኛል፡፡

በ2023 ተመራጭ ሜትሮፖሊታን ሚዲያ የመሆን ርዕይን የሰነቀው አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ፣ ተወዳደሪነት እና ተመራጭነቱን ለማሳደግ የጀመራቸውን የለውጥ ሥራዎች በማሳደግ የአድማጭ፣ ተመልካች እና አንባቢዎቹን ፍላጎት በማርካት የትውልድ ድምጽነቱን ለማረጋገጥ እየተጋ ነው፡፡ ለዚህም ከወቅቱ ጋር የሚሄዱ፣ የነዋሪዎች ድምጽ እንዲስተጋባ የሚያደርጉ፣ እያዝናኑ የሚያስተምሩ ይዘቶችን ቀርጾ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ እነዚህ እና መሰል ተግባራት አድማጭ፣ ተመልካችና አንባቢ ከማግኘት ባለፈ የተለያዩ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከሚዲያው ጋር የመስራት ፍላጎታቸው እየጨመረ እንዲሄድ አድርገዋቸዋል፡፡

ከሚሰራባቸው ጉዳዮች መካከል አገልግሎት አሰጣጡ አንዱ ነው። በትናንትናው ዕለትም ሚዲያውን ጨምሮ 12 ተቋማት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል ጥምረት ፈጥረዋል። በፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ የሚመራው  ጥምረት “አገልግሎትና ቴክኖሎጂ ክላስተር” የተሰኘ ነው።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የፐብሊክ ሰርቪስ እና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ጀማሉ ጀምበር (ዶ/ር) በዕለቱ ባደረጉት ንግግር፣ “ጥምረቱ ከዚህ ቀደም በተናጠል ይከናወኑ የነበሩ ስራዎችን በጥምረት ማከናወን ውጤታማ እንደሚያደርግ ታምኖበት የተከናወነ ነው። በከተማ ደረጃ በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት ይህ ክላስተር አስፈላጊነቱ ታምኖበት ተደራጅቷል፤ በአገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ላይ ድርሻ ያላቸው ተቋማትም ተካትተዋል” ብለዋል

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክም የህዝብ ድምፅነቱን በማስቀጠል የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማስፋት፣ አገልግሎቱን በገለልተኝነት ለመፈተሽ እና ሎሎች ስራዎችን ለማከናወን ኃላፊነትን በመረከብ ስምምነቱን ፈርሟል።

ይህን አስመልክቶ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ካሣሁን ጎንፋ ባደረጉት ንግግር፤ “ተቋማችን ከዚህ ቀደም የሚነሱ የሕዝብ ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችሉ እንደ ‘አገልጋዩ’ የመሳሰሉ ፕሮግራሞችን እያዘጋጀ ለአድማጭ ተመልካች ሲያደርስ ቆይቷል። አሁን የተፈራረምነው ስምምነት ይህንን ሥራችንን አጠናክረን ለማስቀጠል የሚያስችል ነው፡፡ ስምምነቱን እንደ መልካም ዕድል በመጠቀም ተቋማት የተቋቋሙበትን ተልዕኮ በአግባቡ እንዲወጡ እና ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዲሰጡ፣ ተግባራትን በቅንጅት እንዲፈፅሙ፣ የመልካም አስተዳደር ችግሮች ሲፈጠሩ ደግሞ ክትትል በማድረግ አስቸኳይ ምላሽ እንዲያገኙ የሚያስችል ሁኔታ በመፈጠሩ ሚዲያችን በአግባቡ ይጠቀምበታል” ብለዋል፡፡

ከቀናት በፊት፣ ማለትም ታህሣስ 7 ቀን 2018 ዓ.ም.  ደግሞ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ እንዲሁም ከቴዲ ስቱዲዮ ባለቤት፣ ስራ አስኪያጅና የፊልም ባለሙያ ቴዎድሮስ ተሾመ ጋር ለመሥራት የሚያስችሉ ስምምነቶችን መፈራረም ችሏል፡፡ ስምምነቶቹም አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በጋራ የሚሠሯቸዉን ዋርካ እና መሰል ፕሮግራሞችን ለማጠናከር እንዲሁም በመዝናኛው ዘርፍ “ውብ አዲስ” የተሰኘ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ይዞ ለመቅረብ የሚያስችሉ ናቸው፡፡

በስምምነት ፊርማው ላይ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ሀፍታይ ገብረ እግዚአብሔር፣ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ የአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያው ልሳን እና የሀገር ድል አብሳሪ በመሆን የትውልድ ድምጽነቱን በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል፡፡ የአዲስ አበባን ልማት በማጉላት የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶች ተገቢው ምላሽ ይሰጣቸው ዘንድ በሕዝብና በመንግስት መካከል ድልድይ ሆኖ እያገለገለ ነው ብለዋል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ሁነኛ የሕዝብ ጥያቄዎችንና ቅሬታዎችን በማንሳት የተለያዩ ዝግጅቶችን በተከታታይነት እያቀረበ ያለውን እንደ ዋርካ እና መሰል የህዝብ አንደበት የሆኑ ሥራዎች በተሻለ መልኩ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ቢሮው ድጋፉን እንደሚያደርግም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡

የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ካሳሁን ጎንፋ በበኩላቸው፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ከብቁ የሰው ኃይል ጋር በማቀናጀት የአዲስ አበባ የመረጃ ምንጭ፣ በሀገር አቀፍ ደረጃ ደግሞ ተወዳዳሪ ሚዲያ እየሆነ መምጣቱን በመጠቆም፤ ሚዲያው የይዘት ማሻሻያ ከማድረግ ጀምሮ በተለያዩ ዘርፎች በሠራቸው ሥራዎች አሁን ላይ የአዲስ አበባ የመጀመሪያ የመረጃ ምንጭ እና ትውልድ ተሻጋሪ የመረጃ ቋት መሆን እና ተመራጭነቱን እና ተወዳዳሪነቱን በተግባር እያረጋገጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለሚዲያው ስኬታማ ጉዞ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ድጋፍ ጉልህ መሆኑን የገለጹት ዋና ስራ አስፈፃሚው፤ በቀጣይም ሚዲያው የሕዝብና የመንግስት የመረጃ ፍሰት መደላድልነቱን አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል፡፡ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ በቅንጅት መሥራት እውነተኛ መረጃን የማድረስ፣ በመንግስት እና በሕዝብ መካከል የጋራ ተግባቦት የመፍጠር ወሳኝ ዓላማን ለማሳካት እንደሚያግዝም አንስተዋል፡፡

ይህ የህዝብ ድምጽነት በተለያዩ ፈርጆች ተጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑን በመዝናኛ በኩል እየተሰሩ ያሉ ስራዎች ማሳያዎች ናቸው፡፡ ዋና ስራ አስፈጻሚው በአስተያየታቸው፣ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ እና የቴዲ ስቱዲዮ ባለቤት፣ ስራ አስኪያጅና የፊልም ባለሙያ ቴዎድሮስ ተሾመ በጋራ ለመሥራት የሚያስችላቸውን ስምምነት ማድረጋቸው ለዚህ ጉልህ ተጠቃሽ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ፒያሳ በሚገኘው የአራዳ ፓርክ የፊርማ ስነ- ሥርዓቱ የተከናወነው “ውብ አዲስ” የተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ በይዘት፣ በአቀራረብ፣ በባለሙያ እና መሰል ጉዳዮች ላይ በፊልም ኢንዱስትሪው ዘርፍ አዳዲስ ነገሮችን ሊያስተዋውቅ የሚችል ስለመሆኑ ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል፡፡

“ውብ አዲስ” ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ፤ 4 ሲዝንና 52 ኤፒሶድ እንደሚኖረው የተነገረ ሲሆን ሙሉ ለሙሉ በድርጊት የተሞላ ልብ አንጠልጣይ የቴሌቭዥን ድራማ እና በሁለት ትይዩ ታሪክ (Parallel plot) የሚተረክ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡ ቀረፃው ዘጠና ከመቶ የሚሆነው በአዲስ አበባ የሚከናወን ሲሆን፤ ቀሪው አሥር በመቶው ከአዲስ አበባ ውጭ በሞሮኮ እና ጋና ይከናወናል። በዚህም የሁለቱ ሀገራት የጥበብ ባለሙያዎች ወደ አዲስ አበባ መጥተው ይሳተፋሉ ተብሏል። አዳዲስ ተሰጥዖ ላላቸው ተዋናዮች ትልቅ አጋጣሚ የሚፈጥር፣ ህዝብ እያያቸው በቴሌቪዥን በሚተላለፍ ውድድር በችሎታቸው ብቻ ለትወና ተመርጠው የሚሳተፉበት፣ ጥበበኞችን ወደ ሥራው ማስገባት የሚችል የጥበብ ፕሮጀክት መሆኑም ተነግሯል፡፡

በስምምነት ፊርማው ላይ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ካሣሁን፤ “ይህ ድራማ በይዘቱ እና በአቀራረቡ የከተማዋን ነዋሪ ማህበሰረብ የሚመጥን ነው፡፡ ከተማዋ እያደገች፣ እኛ ትላንት በሠራነው ተገድበን መቆም የለብንም፡፡ የተለያዩ አማራጮችን በመጠቀም፣ የሕዝቡን ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ የተለያዩ ሥራዎችን በማቅረብ የበለጠ ተደራሽ ለመሆን እንሠራለን” ብለዋል፡፡ የአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ አድማጭ ተመልካቾች በቤታቸው ሆነው በጉጉት በመጠበቅ ሊከታተሏቸውና ሊመለከቷቸው የሚችሉ ይዘቶችን ይዞ እየመጣ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

ዋና ሥራ አስፈፃሚው አቶ ካሳሁን አክለው እንዳብራሩት፤ አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ በመዝናኛው ዘርፍ አዲስ ታለንት ሾው፣ ቅዳሜን ከእኛ ጋር በሚሉ እና መሰል መሰናዶዎቹ ሕብረተሰቡን እያዝናና መልዕክት በማስተላለፍ ላይ ይገኛል፡፡ አዳዲስ ባለተሰጥዖ ወጣቶች ሥራቸውን ለሕዝብ በማሳየት ተሰጥኦቸውን ማሳደግ እንዲችሉ የበኩሉን ሚና እየተወጣ ይገኛል፡፡ ይህ ግን በቂ አይደለም፡፡ ከዚህ አንፃር “ውብ አዲስ” የተሰኘው ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ የሕዝብን ፍላጎት በመመለስ የሚዲያውን ተደራሽነት ለማሳደግ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

የ™ውብ አዲስ∫ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማን በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ለማስተላለፍ የሚያስችለውን ዕድል በይፋ በወጣ ጨረታ ላይ ተወዳድሮ ማግኘቱን የጠቆመው አርቲስት ቴዎድሮስ፣ ለውጥ እና አዲስ ነገር ለመፍጠር በአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከአመራሩ ጀምሮ እስከ ሠራተኛው ያለው ተነሳሽነት የሚደነቅ ነው፡፡ ይህ የሚዲያው ለውጥ ለዓመታት ዝግጅት ሲደረግበት የቆየውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ከተቋሙ ጋር ለመሥራት እንዳስወሰነው ተናግሯል፡፡

አዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ከተቋማት ጋር መሥራት የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት ተፈራርሞ የተለያዩ ስራዎችን እንደሰራ፤ አሁንም በመሥራት ላይ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡ ለአብነት ያክል፡- ሥራና ክህሎት፣ ቤቶች ልማትና አስተዳደር፣ ትምህርት፣ ገቢዎች፣ ትራንስፖርት ቢሮዎች፣ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን የመሳሰሉት ተቋማት ጋር የሚሠራቸውን ሥራዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡  

በደረጀ ታደሰ

  

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review