AMN – ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ተግባራዊ የተደረገው ተቋማዊ ሪፎርም፣ የከተማዋን እድገት የሚመጥንና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የአደጋ መከላከል አቅም ለመገንባት ማገዙን የአዲስ አበባ እሳትና አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር መስፍን አያሌው በተለይ ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ እንደገለጹት፤ ተቋሙ ባከናወነው ሪፎርም አዳዲስ አሰራሮችን በመተግበር ቀደም ሲል ከህዝብ ይነሱ የነበሩ ቅሬታዎችን መፍታት አስችሏል ብለዋል።
የምክትል ኮሚሽነሩ እንዳመለከቱት፣ ቀደም ሲል ወደ አደጋ ማሳወቂያ ስልክ ቁጥር 939 ሲደወል “መስመር ይያዛል” በሚል ይቀርብ የነበረውን ቅሬታ ለመፍታት አዲስ ሶፍትዌር ስራ ላይ ውሏል።

አዲሱ አሰራር ማንኛውንም የጥሪ መረጃ ሪከርድ በማድረግ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል እንደሆነም ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
በተጨማሪም አደጋ በሚከሰትበት ስፍራ የሚከናወኑ የነፍስ አድንና የአደጋ መከላከል ስራዎችን በማዕከል ሆኖ በቪዲዮ መከታተል የሚያስችል አሰራር መጀመሩን ገልጸው፤ ይህም ችግሮች ሲያጋጥሙ በቦታው ሳይገኙ በቅጽበት መፍትሄ ለመስጠት ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን አብራርተዋል።
በከተማዋ እየተከናወነ ያለው የኮሪደር ልማት ለተቋሙ ስራ መሳለጥ የጎላ ሚና እያበረከተ እንደሚገኝ ምክትል ኮሚሽነር መስፍን አያሌው ተናግረዋል።
የተጨናነቁ ሰፈሮች መዘመናቸውና መንገዶች መስፋታቸው የአደጋ ጊዜ ተሽከርካሪዎች ወደ ቦታው የሚደርሱበትን ጊዜ በእጅጉ አሳጥሮታል ብለዋል።
በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት ከ200 በላይ የውሃ መቅጃዎች (Hydrants) በመንገዶች ላይ መተከላቸውን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ ይህም ለዓመታት የነበረውን የእሳት ማጥፊያ ውሃ አቅርቦት ችግር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚያቃልለው አስታውቀዋል።
በሽመልስ ታደሰ