በኦሮሚያ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ወስደዋል

You are currently viewing በኦሮሚያ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ወስደዋል

‎AMN ታኅሣሥ 13/2018 ዓ.ም

‎በኦሮሚያ ክልል ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና መዉሰዳቸዉን የኦሮሚያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

‎የኦሮሚያ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መኮንን በየነ ፣ በክልሉ 580 ሺህ የመንግስት ሰራተኞች፣ 190 ሺህ ተማሪዎች፣መምህራን እና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በድምሩ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰልጥነው የምስክር ወረቀት ማግኘታቸውን ጠቁመዋል።

‎የስልጣናዉ ዋና አላማ ወጣቶችን በማብቃት በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የስራ ዕድል እንዲያገኙ ለማስቻል እንደሆነ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተው፣ ኢንቨስትመንትን ወደ ሀገር ውስጥ ለመሳብና ለወጣቶች አቅም ግንባታ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

‎በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነና በቴክኖሎጂ የበለጸገ ትዉልድ ከመገንባት ረገድም ስልጠናዉ ትልቅ ጠቀሜታ ይኖረዋል ብለዋል ፡፡

‎በክልሉ የመንግስት አገልግሎትን ዲጂታላይዝ በማድረግ ቀልጣፋ፣ ጥራት ያለውና ከወረቀት ንክኪ ነፃ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፣ 123 አገልግሎቶችን በኢንተርኔት (online) ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‎ይህ አሰራር ከአንድ አመት ከስድስት ወር በኃላ በ23 ከተሞችና በ2 ዞኖች እንደሚተገበር ገልጸዋል።

‎ኦሮሚያን ዲጂታላይዝ የማድረግና የመንግስት አገልግሎትን እስከ ቀበሌ የማድረስ ስራ እየተሰራ በመሆኑ፣ ተገልጋዩም በቴክኖሎጂ ራሱን ማላመድና ማብቃት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡

‎በክልሉ 5 ከተሞች የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትም የኦሮሚያ ዲጂታል ስትራቴጂ 2030 ትግበራ አካል መሆኑንም ጨምረዉ አብራርተዋል፡፡

‎ አዲስ እና ትልቅ የዳታ ማዕከል (Data Center) በክልሉ ለመገንባት ግንባታውን የሚያከናውን ኢንተርፕራይዝ መመስረቱንም መናገራቸዉንም የኦሮሚያ ኮሚኒኬሽን ቢሮ ለኤኤምኤን የላከዉ መረጃ ያመላክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review