ለሀገራዊ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሄዎችን ያማከለ የልማት መደላድል ተፈጥሯል

You are currently viewing ለሀገራዊ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሄዎችን ያማከለ የልማት መደላድል ተፈጥሯል

AMN – ታኀሣሥ 14/2018 ዓ.ም

በባለፉት አምስት ዓመታት መንግስት የስታርትአፕ አዋጅን በማጽደቅ ለሀገራዊ ችግሮች ሀገር በቀል መፍትሄዎችን በማምጣት የመንግስትና የግል ዘርፍ አጋርነትን ያማከለ የልማት መደላድል መፍጠር መቻሉን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዲጂታል ሥነ-ምህዳሩን ሙሉ በሙሉ ለማስፋት የተለያዩ አስቻይ ፖሊሲዎችና የሕግ ማዕቀፎች ተዘጋጅተው ወደ ሥራ መግባቱ የዘርፉን እድገት እንዲፋጠን አስችሏል ብለዋል።

በዚህ መሠረት “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” የትግበራ ምዕራፍ በይፋ ተጠናቆ፣ ሀገራችን ወደ “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሯን ተናግረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ሂደት የወጣቶች የአስተሳሰብና የስራ ባህሪ መቀየሩን ገልጸው፣ ይህን የተቀየረ እሳቤ መሠረት በማድረግ ወደ አዲስ የዲጂታል ልማት ምዕራፍ መሸጋገር አስፈላጊ መሆኑን አስረድተዋል።

“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” ስትራቴጂ በሁሉም ዘርፎች የተጀመሩ የዲጂታል ፕሮጀክቶችን በፍጥነት ለማስፋፋት፣ ተናባቢ የዲጂታል ሥነ-ምህዳር ለመገንባት እና ዘላቂ ሀገራዊ ትራንስፎርሜሽንን ለማረጋገጥ የተነደፈ መሆኑን ተናግረዋል።

መንግስት ብሔራዊ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ምክር ቤትን በ“ዲጂታል ኢትዮጵያ 2025” በማቋቋም ወደ ሥራ መገባቱን አስታውሰው፣ ምክር ቤቱ በባለፈው አንድ ዓመት ብቻ ከ68 ነጥብ 7 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ አላግባብ ይፈፀም የነበረ ወጪን ማስቀረት መቻሉን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ብሔራዊ የመረጃ ትንተና ሥርዓት መጀመሩን ጠቁመው፣ ከተለያዩ ምንጮች መረጃ በመሰብሰብ ለተፈቀዱ ተጠቃሚዎች የትንታኔ ሪፖርቶችና ዳሽቦርዶችን የሚያቀርብ ሀገር በቀል የቴክኖሎጂ መፍትሄ ሥራ ላይ መዋሉን ገልጸዋል።

በመጨረሻም “ዲጂታል ኢትዮጵያ 2030” የሚሳካው መንግስት፣ የግሉ ዘርፍ፣ ማህበረሰብና ግለሰቦች በጋራ በመተባበር ሲሰሩ ብቻ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ አስገንዝበዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review