ኢትዮጵያ የዲጂታል 2030 ጉዞዋን የሚያፋጥንና የወሳኝ ኩነት ምዝገባን እንዲሁም የነዋሪነት አገልግሎት አሰጣጥን ሥር ነቀል በሆነ መልኩ የሚቀይር አዲስ የዲጂታል ሲስተም ይፋ አድርጋለች።
የአርተፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ታዬ ግርማ (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ይህ አዲስ ሲስተም በሀገር በቀል ተቋም እና በሀገር ልጆች የበለጸገ ሲሆን፣ በሀገር ውስጥ ባለሙያዎች በጥራትና በፍጥነት ሥራዎችን ማከናወን እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
ቴክኖሎጂው ከወረዳ እስከ ማዕከል ያለውን የአገልግሎት ሰንሰለት በማስተሳሰር በክልል፣ በከተማ፣ በዞንና በወረዳ ደረጃ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ወጥና እርስ በርስ የተናበቡ እንዲሆኑ ያደርጋል።
አዲስ የተዘጋጀው ሲስተም የቤተሰብ ምዝገባን፣ የልደት፣ የጋብቻ እና የሞት ኩነቶችን እንዲሁም የነዋሪነት እና የዝምድና ማረጋገጫ አገልግሎቶችን በአንድ ቋት ውስጥ እንደሚይዝም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል። በሂደቱ የሚዘጋጁ ሰነዶች ትክክለኛነትን የሚያረጋግጥ ዘመናዊ የክትትል ዘዴ እንደተካተተበትም ተገልጿል፡፡
ሲስተሙ የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን በቀጥታ የሚያገናኝ ሲሆን፣ በጤና ተቋማት የሚከሰቱ ልደቶችና ሞቶች፣ እንዲሁም በፍርድ ቤት የሚወሰኑ የፍቺና የጉዲፈቻ ጉዳዮች መረጃ ወዲያውኑ ለወሳኝ ኩነት አገልግሎት ሰጪዎች እንዲደርሱ ያደርጋል።

ዜጎች አገልግሎቱን ለማግኘት የግድ መገኘት ሳይጠበቅባቸው በፐብሊክ ፓርታሉ በኩል ባሉበት ሆነው አገልግሎት መጠየቅ ይችላሉ ተብሏል።
በተለየ ሁኔታ በተዘጋጀ ሞባይል አፕሊኬሽን አማካኝነት ዲጂታል ሰነዶቻቸውን መያዝ እና ለሚፈልጉት አካል ማሳየት እንደሚቻልም ተገልጿል፡፡
ተገልጋዮች በአገልግሎት አሰጣጡ ላይ ያላቸውን ቅሬታ ወይም አስተያየት በሲስተሙ በኩል ወዲያውኑ ማስተላለፍ እንደሚችሉም ምክትል ዋና ዳይሬክተሩ ታዬ ግርማ (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ሲስተም ስኬታማነት እስካሁን 350 ባለሙያዎች አስፈላጊውን ስልጠና ወስደው ወደ ሥራ መግባታቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ሲስተሙ አመራሮች የአገልግሎት አሰጣጡን በየደረጃው እንዲቆጣጠሩ የሚያስችል የዳሽ ቦርድ (Dashboard) ቁጥጥርም ተካቶበታል ተብሏል፡፡
ይህ ቴክኖሎጂ ኢትዮጵያ ለጀመረችው የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ እንደ ትልቅ ስኬት የሚቆጠር መሆኑን ታዬ ግርማ (ዶ/ር) አክለው ገልጸዋል።
በአስማረ መኮንን