በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 1 መቶ 28 ሚሊዮን ለማድረስ ይሰራል

You are currently viewing በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር 1 መቶ 28 ሚሊዮን ለማድረስ ይሰራል

AMN-ታኅሳስ 14/2018

ዲጂታል መሠረተ ልማትና ኤሌክትሪክሲቲ ለአንድ ሃገር የዲጂታል ልማትና ኢኮኖሚ ፈጣን ግንባታ መሠረታዊ መሆናቸውን የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ስራ አስፈፃሚ ወ/ሪት ፍሬህይወት ታምሩ ገልፀዋል።

የዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በቴሌኮም ዘርፉ ባለፍት 5 ዓመታት በርካታ ስኬታማ ተግባራት መከናወናቸውን ያነሱት ዋና ስራ አስፈፃሚዋ፤ 97 ሚሊዮን የቴሌኮም አገልግሎት ተጠቃሚዎች ብሎም 57 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎች ማሳያ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ከ1 ሺህ 30 በላይ በሚሆኑ ከተሞች የ4ጂ አገልግሎት ብሎም በ27 ከተሞች የ5ጂ ኔትዎርክ ተጠቃሚ እንዲሁኑ መደረጉ ዲጂታል ኢትዮጵያን 2030 ዕውን ለማድረግ መሠረት የጣሉ ተግባራት ናቸውም ብለዋል፡፡

በተለይም 78 በመቶ የደረሰው የሞባይል ተጠቃሚዎች ቁጥር ለዲጂታል ኢኮኖሚ ተጠቃሚነትም እያበረከተ ያለው ሚና ጉልህ መሆኑን ወ/ሪት ፍሬህይወት ተናግረዋል፡፡

የዲጂታል ሞባይል ዋሌት አካውንት ወይም ቴሌ ብር አካውንት ቁጥር ተጠቃሚዎች 1 መቶ 61 ሚሊዮን መድረሱንሥራ አስፈፃሚዋ አንስተው፤ 18 ትሪሊየን ብር የሚሆን የገንዘብ ዝውውር ወይም 82 በመቶ የጂዲፒ ገንዘብ ዝውውር መደረጉን አብራርተዋል።

ይህም ድምር ውጤቱ ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 አስቻይ ሁኔታዎች መኖራቸውን በተግባር ያሳየ ነው ብለዋል።

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ተደራሽነትና አካታችነትን በማስፈን በቀጣይ አምስት አመታት የሞባይ ተጠቃሚዎችን ቁጥር 128 ሚሊዮን ማድረስ፣ 87 ሚሊዮን የኢንተርኔት ተጠቃሚዎችን ለማሳደግ ራዕይ ተይዟል ሲሉ ስራ አስፈፃሚዋ ተናግረዋል።

የ5 ጂ ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥርም ከአንድ መቶ በላይ ማድረስ ብሎም 98 በመቶ የሚሆኑ የመንግስት ተቋማት አገልግሎትም ኦንላየን የማድረስ ትልም መያዙን ገልፀዋል።

በሚካኤል ኅሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review