የኢትዮጵያ አደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን በትግራይ ክልል ሰሜን ምዕራብ ዞን፣ አስገደ ወረዳ፣ ሕፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች የሰብአዊ ድጋፍ አቅርቦትን በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫውም፣ መንግሥት በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረት በማድረግ የምግብ ሰብአዊ ድጋፍ እያቀረበ እንደሚገኝ ገልጿል።
ሆኖም በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች በሕፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎች የሰብአዊ ድጋፍ እንዳልደረሳቸው የሚገልጽ የተሳሳተ እና የመጠለያ ጣቢያውን አጠቃላይ ሁኔታ የማይገልጽ ዘገባ ሆኖ መገኘቱን ኮሚሽኑ አስታውቋል።
የሰብዓዊ ድጋፍን በሚመለከት በመደበኛነት ዓመቱን በሙሉ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የምግብ ስርጭት ሳይቆራረጥ እየተከናወነ መሆኑን ኮሚሽኑ ለኤ ኤም ኤን በላከው መግለጫ አመላክቷል።
“በሕፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያም የሚገኙ ዜጎቻችን ዓመቱን ሙሉ ተመሳሳይ ድጋፍ ሲደረግላቸው የነበረ ሲሆን፣ ከመስከረም ወር 2018 ጀምሮ እስከ ታኅሣሥ ወር 2018 ድረስ የተሟላ እና ያልተቆራረጠ የምግብ ሰብአዊ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን መረጃዎቻችን ያሳያሉ” ብሏል።
በአስገደ ወረዳ ሕፃፅ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያ ባለፉት አራት ወራት የተደረገውን ድጋፍ በቁጥር ለመግለጽ፣ 14 ሺህ 413 ዜጎች ድጋፍ ሲደረግ ቆይቷል።
በተጨማሪም ከአጎራባች መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ዜጎችን ጨምሮ በመስከረም ወር 16 ሺህ 775፣ በጥቅምት ወር 18 ሺህ 290፣ በኅዳር ወር 17 ሺህ 813 እንዲሁም በታኅሣሥ ወር የሚያስፈልገው ለ14 ሺህ 413 ዜጎች የሚያስፈልግ ምግብ ተሰራጭቷል ሲል በዝርዝር አስቀምጧል።
በዚህም በድምሩ 11 ሺህ 406 ኩንታል ምግብ (ስንዴ፣ ማሽላ፣ ጥራጥሬ እና የምግብ ዘይት) ባለፉት አራት ወራት እንዲዳርሳቸው ተደርጓል። ይህ ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከ257 ሚሊዮን (ከሁለት መቶ አምሳ ሰባት ሚሊየን) ብር በላይ እንደሚሆን ገልጿል።
በሌላ በኩል በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር የተለያዩ የሰብአዊ ድጋፍ ችግሮች መኖራቸውን እና ተጨማሪ የፌዴራል ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ቢጠየቅ ኖሮ በኮሚሽናችን በኩል አስፈላጊውን ድጋፍ ለመፈጸም የሚያስችል ዝግጁነት ያለን መሆኑን ለመግለጽ እንወዳለን ሲል በመግለጫው አስታውቋል።
ኮሚሽኑ ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ ለተፈናቃይ ማኅበረሰብ የሚላከው ድጋፍ ለታለመለት ዓላማ ብቻ መዋሉን የማረጋገጥ እና ክፍተቶች ቢኖሩም እንዲሟላ የማድረግ ኃላፊነት የክልሉና የአካባቢው ጊዜያዊ አስተዳደር መሆኑን ለማሳሰብ እንወዳለን ብሏል።