እየጎለበተ ያለው የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪዎች አቅም

You are currently viewing እየጎለበተ ያለው የአዲስ አበባ ኢንዱስትሪዎች አቅም

በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ አራት ወራት ኢንዱስትሪዎቹ 5 ሚሊዮን 53 ሺህ 487 ቶን ተኪ ምርቶችን ለሀገር ውስጥ ገበያ አቅርበዋል

ኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ዘርፍ ጋር በመተዋወቅ ረገድ ረጅም ዕድሜ አስቆጥራለች፡፡ ይሁን እንጂ ያለፈችበት ጉዞ የኢንዱስትሪው ዘርፍ የዕድሜውን ያክል ውጤት እንዳያመጣ አድርጎ ቆይቷል፡፡ ነገር ግን ከትንሽ እስከትልቅ የኢንዱስትሪ ምርቶችን በከፍተኛ ደረጃ ከውጭ ሀገር በማስገባት ትጠቀማለች፡፡ በዚህ ምክንያት ለምርት ግዢ ለከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ወጪ ስትዳረግ ቆይታለች፡፡

ረጅም ዘመናትን በተሻገረ ሂደት ውስጥ እንደ ሀገር በሚደረገው የገቢና የወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ምጣኔ ላይ፤ የገቢ ምርቶች መጠን ከወጪ ምርቶች መጠን አብላጫ መያዙ ነው፡፡ ይህንን ትልቅ ክፍተት ለማጥበብ፣ በሂደትም የወጪ ምርቶች ከገቢ ምርቶች አብላጫ እንዲኖራቸው ለማስቻል የመደመር ፍልስፍና አካል የሆነው የሀገር በቀል ኢኮኖሚያዊ እሳቤ እየተተገበረ ይገኛል፡፡

በሀገር ውስጥ ያሉ ኢንዱስትሪዎችን አቅም በማሳደግ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ምርቶችን ተክተው እንዲያመርቱ ማስቻል የሚለው እና ወደ ተግባር ተለውጦ ተጨባጭ ውጤት እያመጣ ያለው የኢንዱስትሪ ልማት እሳቤ በምሳሌነት የሚጠቀስ ነው፡፡ አምራች ኢንዱስትሪዎች እንዲስፋፉ፣ አቅማቸው እንዲያድግ፣ ምርትና ምርታማነታቸው እንዲጨምር እንደ ሀገር ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተሠራው ሥራ ከፍተኛ ውጤት ስለመምጣቱ ሪፖርቶች ያመለክታሉ፡፡

መዲናችን አዲስ አበባም ለዘርፉ ዕድገት የበኩሏን ድርሻ እየተወጣች ስለመሆኑ፤ ከከተማ አስተዳደሩ የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡ እንደ ቢሮው መረጃ ከሆነ፤ በመዲናዋ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው፣ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እየተደረገላቸው ምርት በማምረት ላይ የሚገኙ ኢንዱስትሪዎች ብዛት 3 ሺህ 822 ደርሷል (ይህ መረጃ እስከ ሕዳር 2018 ዓ.ም. ድረስ ያለውን የሚመለከት ነው)፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአምራች ኢንዱስትሪ ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ኩሳ ለአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ለአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በሰጡት ማብራሪያ እንደገለጹት፤ በከተማዋ በሥራ ላይ ካሉ አምራች ኢንዱስትሪዎች መካከል ቁጥራቸው 2 ሺህ 265 የሚሆኑት ከውጭ ሀገር የሚገቡ ተኪ ምርቶችን የሚያመርቱ ናቸው፡፡ እነዚህ ኢንዱስትሪዎች በዋናነት በአራት ንዑስ ዘርፎች ማለትም፡- በቆዳና ጨርቃጨርቅ፣ በእንጨትና ብረታብረት፣ በግብርና ምርት ማቀነባበር ወይም አግሮፕሮሰሲንግ እንዲሁም ኬሚካልና ኮንስትራክሽን ውስጥ የሚካተቱ ሲሆን፤ ኢንዱስትሪዎቹ ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶችን በመተካት ትልቅ አስተዋፅኦ እያደረጉ ነው፡፡

የካቫ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪ እንዲሁም የአልማኪር ጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ኢንዱስትሪ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደረጃ ከውጭ ሀገር የሚገቡ ተኪ ምርቶችን በማምረት ሥራ ከሚገኙት በሺዎች የሚቆጠሩ ኢንዱስትሪዎች መካከል ይካተታሉ፡፡ የዝግጅት ክፍላችንም የእነዚህ አምራች ኢንዱስትሪዎች የሥራ እንቅስቃሴ ምን እንደሚመስል ለመቃኘት ሞክሯል፡፡ በቅኝቱም ኢንዱስትሪዎቹ ተኪ ምርቶችን በማምረት ለዘርፉ ዕድገት የበኩላቸውን ሚና እየተወጡ መሆናቸውን መገንዘብ ችሏል፡፡

ወጣት ቤተል ተካ፤ የካቫና የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራች ድርጅት ሥራ አስኪያጅ ናት፡፡ በ2009 ዓ.ም. በአንድ ማሽንና በአንድ ሠራተኛ ሥራውን የጀመረው ድርጅቱ ዛሬ ላይ በምርቶቹ ለሀገር በሚጠቅም ደረጃ የተገኘበት የዓመታት ጉዞ እንደሆነ ትናገራለች። እንደ ወጣት ቤተል ገለፃ፤ የድርጅቱ መሥራች የአርክቴክት ሙያተኛዋ ሰመሐል ጎሽት ትባላለች፡፡ አጀማመሯም በውስጧ የታመቀውን ዕውቀትና ክህሎት ለመግለጥ የቆዳና ቆዳ ውጤቶች ምርት ሥራ ሁነኛ ዘርፍ ሆኖ ስላገኘችው ነው። በዚህ የተነሳም ሩቅ ሳትሄድ በገዛችው አንድ ማሽን፣ የእናቷን ቤት በመሥሪያ ቦታነት በመጠቀምና ራሷን ሠራተኛ አድርጋ በማሰማራት ሥራዋን አንድ ብላ ጀመረች፡፡ ጅምሯ ሊያድግ የሚችል እንደሆነ በመረዳቷ፤ ተጨማሪ አንድ ማሽንና አንድ ሠራተኛ ወደ ሥራ ቦታው አካተተች፡፡

የስምንት ዓመት ዕድሜ ያስቆጠረው የሰመሐል የሥራ እንቅስቃሴ አሁን ላይ ተስፋ የሚጣልበት ድርጅት ሆኗል፡፡ በ850 ካሬ ባረፈ ሼድ ውስጥ፣ የቆዳና ቆዳ ውጤቶችን ማምረት የሚያስችሉ ዘመናዊ ማሽኖችን በመጠቀም፣ ከ50 በላይ ቋሚ ሠራተኞችን በመቅጠር ምርቶችን ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገራት ገበያዎች በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡ የተለያዩ ቦርሳዎችን፣ የሴት ጫማዎችን፣ የቢሮ መገልገያዎችን፣ የአበባ ማስቀመጫዎችን፣ ለዓለም አቀፍ ስብሰባና ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች የሚቀርቡ የተቋማት ሎጎ የታተመባቸው ቦርሳዎች፣ የፅሕፈት መሳሪያ መያዣዎች እና መሰል ምርቶችን የሚያመርተው የካቫና የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪ ከምርቶቹ መካከል ከ90 ከመቶ በላይ ለውጭ ሀገር ገበያዎች እንደሚያቀርብ የጠቆመችው ሥራ አስኪያጇ፤ ከነዚህም አሜሪካ፣ ሩዋንዳ፣ ጣሊያን፣ ጀርመን፣ ሲውዘርላንድ፣ ካናዳ ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህ ሥራ ለሀገር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ማስገኘት ችሏል፡፡ ለአብነት በ2015 ዓ.ም. ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ ካስገኙ መሰል አምራቾች መካከል የተሻለ ደረጃ በማግኘት ከመንግስት ዕውቅናና ሽልማት ተሰጥቶታል፡፡

“የኢትዮጵያ ቆዳ ምርት በዓለም አቀፍ ደረጃ በጣም ተመራጭ እና ተወዳጅ ነው።” ስለዚህ የቆዳ ምርቶች በጥራትና የዓለም ገበያን ባገናዘበ መልኩ ከተዘጋጁ የምርቱ ገበያ የማግኘት ዕድል ቀላል ነው” ያለችው ወጣት ቤተል፤ ለሥራቸው ውጤታማነት የመንግስት ድጋፍ ከፍተኛ መሆኑን አንስታለች፡፡ ይህም ምቹ የሥራ ቦታ ከመስጠት ጀምሮ ጥራት ያለውን ምርት ለማምረት የሚያስችሉ ማሽኖችን እና መለዋወጫዎችን ከቀረጥ ነጻ እንዲያስገቡ ዕድል ማመቻቸቱን ጠቅሳለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የውጭ ምንዛሬ ገቢ ተጠቃሚነት ላይ የነበረው አሠራር በመሻሻሉ ለአምራቾች ከሚሰጠው ተጠቃሚነት መቋደስ መቻላቸው ለስኬታቸው አጋዥ አቅም እንደሆናቸው አልሸሸገችም፡፡ በቀጣይ ምርታቸውን በብዛት፣ በዓይነት እና በጥራት በማሳደግ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር በዓለም ገበያ ላይ በስፋት ለመሳተፍ ድርጅቱ አቅዷል፡፡

በተመሳሳይ የአልማኪር ጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ድርጅት ተኪ ምርቶችን በማምረት ለሀገር ውስጥ ገበያ እንዲሁም የውጭ ገበያን በመድረስ ከኢንዱስትሪው የሚጠበቅበትን ኃላፊነት እየተወጣ ስለመሆኑ የድርጅቱ መስራችና ሥራ አስኪያጅ አቶ ክብሮም ፍፁም ያስረዳሉ፡፡ እንደ እሳቸው ማብራሪያ፤ ድርጅቱ በ2007 ዓ.ም. የተመሰረተ ነው። ሲመሰረት በ18 ማሽኖች እና በ18 የሠው ኃይል በህትመትና የአልባሳት ስፌት ሥራ ላይ በማተኮር ነበር፡፡ በሂደትም አቅሙን በማሳደግ እና በማሻሻል በአሁኑ ወቅት በ374 ማሽኖች የጨርቃጨርቅና የአልባሳት ምርት ሥራን በስፋት እና በብዛት እያከናወነ ይገኛል፡፡ በዚህም ለ318 ሠራተኞች ቋሚ የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡

የአልማኪር ጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ድርጅት ከምስረታው ማግስት ጀምሮ በምርቶቹ የዓለም ገበያን እንደደረሰ የጠቆሙት አቶ ክብሮም፤ “ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ያለማቋረጥ ምርቶቻችንን ለውጭ ሀገራት ገበያዎች ስናቀርብ ቆይተናል፡፡ የምናቀርበው ከምናመርተው 95 ከመቶ የሚሸፍን ነበር፡፡ ምርቶቻችንን ከምንልክባቸው ሀገራት መካከል ጀርመን፣ ጅቡቲ እና ኡጋንዳ በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ” ብለዋል፡፡

አያይዘው እንዳብራሩት፤ ድርጅቱ ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ፤ ከሚያመርታቸው ምርቶች መካከል 95 ከመቶ የሚሆነውን ከውጭ ሀገራት የሚገቡ ምርቶች በመተካት ለሀገር ውስጥ ገበያ እያቀረበ ይገኛል፡፡ ከምርቶቹ መካከል፡- የወንድ እና የሴት ሸሚዞች፣ ቲሸርቶች፣ የልጆች አልባሳት፣ ጃኬቶች፣ ከረባት ይጠቀሳሉ፡፡ ለውጭ ገበያ ከምናቀርበው ውስጥ 5 ከመቶ የሚሆነውን ምርት የሚይዘው የወንዶች ከረባት ሲሆን የገበያ መዳረሻው ናይጄሪያ ነው፡፡

የአልማኪር ጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ድርጅት አሁን ለደረሰበት ስኬት የከተማ አስተዳደሩ አስተዋፅኦ የላቀ ስለመሆኑ አቶ ክብሮም አልሸሸጉም። ይህንንም አስመልክቶ ሲገልጹ፤ “ከመንግስት 300 ካሬ ሜትር የመሥሪያ ቦታን ጨምሮ የተለያዩ ድጋፎችን አግኝተናል፡፡ ለሠራተኞቻችን የሙያና ክህሎት ስልጠናዎችን (የካይዘን፣ የቴክኖሎጂ፣ የአልባሳት ዲዛይን…) ጋር የተያያዘ ከተግባረ ዕድ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ ተከታታይነት ባለው ሁኔታ ተጠቃሚ ሆነናል፡፡ ከሥራና ክህሎት ቢሮ ጋር በመተባበር የሥራ ላይ ስልጠና የሚወስዱ ወጣቶችን በሥራ ላይ እንዲሰማሩ የሚደረግበት አሠራርም ወጣቶቹንም፣ ድርጅታችንንም ተጠቃሚ እያደረገ ነው፡፡ ከሥራችን ስፋት አንፃር ከመንግስት የተሰጠን መሥሪያ ቦታ ባለመብቃቱ ሌሎች ሁለት ቦታዎችን ተከራይተን እየሠራን እንገኛለን” ብለዋል።

ድርጅቱ በቂ የሆነ የሀገር ውስጥ ተጠቃሚዎች ስላሉ የገበያ ችግር እንደሌለበት አቶ ክብሮም አንስተው፤ በከተማዋ ውስጥ ባላቸው ሁለት ሱቆች (መርካቶ እና ኮልፌ) ምርቶቻቸውን እንደሚሸጡ ተናግረዋል፡፡ የጨርቃጨርቅ እና አልባሳት ዘርፍ አስተማማኝ የገበያ አማራጭ ስላለው፤ ድርጅቱ በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ የማስፋፊያ ሥራ ለማከናወን አቅዷል፡፡ በዚህም የሠራተኞቹን ቁጥር ወደ 3 ሺህ ለማሳደግ ግብ አስቀምጧል፡፡ ለዚህ ውጤት ለመብቃት የመሥሪያ ቦታ ጥያቄ ከመንግስት ምላሽ እንደሚያገኝ ተስፋ በማድረግ እየተጠባበቁ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

የካቫና የቆዳና ቆዳ ውጤቶች አምራች ኢንዱስትሪን እንዲሁም የአልማኪር ጨርቃጨርቅና አልባሳት ማምረቻ ኢንዱስትሪን ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ 2 ሺህ 265 ተኪ ምርት የሚያመርቱ ኢንዱስትሪዎች በማምረት ሥራ ላይ እንደሚገኙ ያነሱት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአምራች ኢንዱስትሪ ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ጳውሎስ ኩሳ፤ ተኪ ምርትን በማምረት እንደ ሀገር ከፍተኛጠቀሜታ እየተገኘ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የራሱን አስተዋፅኦ ማድረጉን አጠናክሮ ቀጥሏል። ለማሳያ ያክል ብናነሳ፡- በ2017 በጀት ዓመት በከተማዋ በማምረት ሥራ ላይ ከነበሩ ኢንዱስትሪዎች 7 ሚሊዮን 461 ሺህ 764 ቶን የሚመዝን ምርት አምርተዋል፡፡ እነዚህንም ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ 1 ቢሊዮን 854 ሚሊዮን 859 ሺህ 224 የአሜሪካ ዶላር ወጪን አስቀርተዋል፡፡

በተመሳሳይ በያዝነው የ2018 በጀት ዓመት፣ የመጀመሪያ አራት ወራት ውስጥ ኢንዱስትሪዎቹ 5 ሚሊዮን 53 ሺህ 487 ቶን ተኪ ምርቶችን አምርተው ለሀገር ውስጥ ገበያ አቅርበዋል፡፡ በዚህም እንደ ሀገር ይወጣ የነበረውን 613 ሚሊዮን 426 ሺህ 791 የአሜሪካ ዶላር አስቀርተዋል፡፡ የአራት ወራቱ አፈጻጸም እንደሚያሳየው እንደ ከተማ የዘንድሮው አፈፃፀም ከአምናው የተሻለ እንደሚሆን የሚያመላክት ነው፡፡

አቶ ጳውሎስ በማብራሪያቸው፤ በአሁኑ ጊዜ እንደ ከተማ የአምራች ኢንዱስትሪዎች የማምረት አቅም 66 ነጥብ 6 ከመቶ ደርሷል፡፡ ይህንን በ2022 በጀት ዓመት ወደ 85 ከመቶ ለማድረስ ታቅዶ እየተሠራ ነው፡፡ የማምረት አቅም ማለት፡- ኢንዱስትሪዎቹ ያላቸውን የሠው ኃይል፣ የመሥሪያ ቦታ፣ ማሽን፣ ካፒታል፣ ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም ማምረት ከሚጠበቅባቸው ከፍተኛ መጠን ውስጥ በተጨባጭ ያሳኩት ምን ያክል እንደሆነ የሚያመላክት ነው፡፡

ኢንዱስትሪዎች ከሚያመርቷቸው ተኪ ምርቶች መካከል፡- የተማሪ የትምህርት ቁሳቁሶች (ደብተር፣ እስክርቢቶና እርሳስ)፣ የተማሪ የደንብ ልብስና ቦርሳዎች፣ የተለያዩ ተቋማት ሠራተኞች የሥራ (የደንብ) ልብሶች፣ የፀጥታ አካላት አልባሳት እና ጫማዎች፣ የንፅህና እና የፅዳት መጠበቂያ ግብዓቶች፣ በኮሪደር ልማቱ ጥቅም ላይ የዋሉ የመንገድ ዳር መብራት ፖሎች (የመጀመሪያ ዙር ላይ ከቻይና ከመጣው በስተቀር)፣ የእብነበረድ (ግራናይት)፣ የቢሮ መገልገያ ፈርኒቸሮች እና መሰል ምርቶችን በሀገር ውስጥ መተካት የተቻለበትን ሁኔታ ማንሳት ይቻላል፡፡

ኢንዱስትሪዎች የሚያመርቷቸው ተኪ ምርቶች በገበያ ላይ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ቢሮው ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመተባበር ጠንካራ ድጋፍና ክትትል እንደሚደረግላቸው ያነሱት የአምራች ኢንዱስትሪ ድጋፍ ዘርፍ ኃላፊ፤ በተለይ ምርታቸው ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃውን የጠበቀ እንዲሆን በኢትዮጵያ የተስማሚነት ምዘና ድርጅት የተዘጋጀውን የጥራት መመዘኛ መስፈርት እንዲያሟሉ መደረጉን ጠቅሰዋል፡፡

በደረጀ ታደሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review