6ኛው የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ዛሬ ባካሄደው 6ኛ መደበኛ ስብሰባ የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል፡፡
የአዋጁን አስፈላጊነት በሚመለከት የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት እንዲሁም የፕላን፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴዎች በጋራ ያዘጋጁትን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ የውሃ፣ መስኖ፣ ቆላማ አካባቢ እና አካባቢ ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወ/ሮ ፈቲያ አህመድ አቅርበዋል፡፡
ሥርዓተ ምህዳሮች ዘላቂነታቸው ባልተረጋገጠ መንገድ ጥቅም ላይ እየዋሉ እና በተፈጥሮ ማገገም ከሚችሉት በላይ እየተመናመኑ የመጡ መሆኑ፤ በተለያዩ የዓለም ክፍሎች በሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ዋጋ ላይ የተፈጠረው ሳይንሳዊ ግንዛቤ ማደግ ለአዋጁ መውጣት መነሻ ምክንያት መሆኑን በውሳኔ ሀሳቡ ተጠቅሷል፡፡
የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎቶች ለኢኮኖሚ የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ በፖሊሲዎችና በውሳኔ አሰጣጥ ላይ እየተንጸባረቀ የሚገኝ መሆኑንም ተገልጿል።
በመሆኑም የሥርዓተ ምህዳርን በዘላቂነት ለማስተዳደር የሚያስችል የሥርዓተ ምህዳር አገልግሎት ክፍያ የህግ ማዕቀፍ እና የአሰራር ስርዓቶችን መዘርጋት አስፈላጊ በመሆኑ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ መሆኑን ወ/ሮ ፈቲያ ባቀረቡት የውሳኔ ሀሳብ ገልጸዋል፡፡
የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው የአዋጁን አስፈላጊት በሚመለከት አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን፤ በቀጣይ አፈፃፀም ላይ ትኩረት ሊደረግ ይገባል ያሏቸውን ሀሳብ አቅርበዋል።
በመጨረሻም ምክር ቤቱ የቀረበውን ረቂቅ አዋጅ ቁጥር 1401/2018 አድርጎ በአንድ ድምፅ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል።