በአዲስ አበባ የፈነጠቀው አዲሱ የቤት ብርሃን

You are currently viewing በአዲስ አበባ የፈነጠቀው አዲሱ የቤት ብርሃን

በአዲስ አበባ ሰማይ ስር እየበቀሉ ያሉት አዳዲስ የመኖሪያ ሕንጻዎች እየተገነቡ ነው ከሚባል እየተመረቱ ነው ቢባል ይቀላል። የከተማዋ ነዋሪዎችን ለዓመታት የቆየ የመኖሪያ ቤት ጥያቄ በዘላቂነት ለመመለስ ሌት ከቀን እየሠራ የሚገኘው የከተማ አስተዳደሩ ከተለመደው አዝጋሚ የግንባታ አካሄድ በመውጣት በአዲስ ቴክኖሎጂ በመታገዘ ጥራትን ከፍጥነት ጋር አጣምሮ ከአንድ ዓመት ባነሰ ጊዜ ውስጥ 100 ሽህ ቤቶችን ገንብቶ ለማጠናቀቅ ታላቅ ዘመቻ ላይ ይገኛል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አስተባባሪነት የተጀመረውና በ18 ሳይቶች እየተከናወነ በሚገኘው አዲስ የግንባታ ታሪክ ላይ የግል ባለሀብቶች እንዲሁም ማሕበራት ጭምር የመንግስት እና የግል ዘርፍ አዲስ የትብብር ማሕቀፍ ጀምረዋል። በተለይ ደግሞ በገላን ጉራ እና በቱሉ ዲምቱ ሳይቶች ላይ የተጀመሩት ግንባታዎች ማርሽ ቀያሪ የሚባሉ ሆነዋል።

በ6 ቀናት አንድ ወለል እየተገነባ ነው

በገላን ጉራ ሳይት እየተከናወነ ያለው ትዕይንት ትንግርት የሚባል ነው። 13 ወለል ያላቸው 6 ሕንጻዎች ግንባታቸው በተጀመረ በአጭር ጊዜ ውስጥ አፈጻጸማቸው 36 በመቶ ደርሷል። እዚህ ሳይት ላይ ግንባታው የሚከናወንበት ፍጥነት አስደናቂ ነው።

ኢንጂነር ታምራት አክሊሉ በአዲስ አበባ ቤቶች ልማት ኮርፖሬሽን የደቡብ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የገላን ጉራ ሣይት አስተባባሪ ናቸው። እርሳቸው ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት ከ5 እስከ 6 ቀናት ባለው ጊዜ ውስጥ አንድ ወለል ተገንብቶ እየተጠናቀቀ ነው። ለዚህም ደግሞ ዋናው ምክንያት ግንባታው እየተከናወነ የሚገኘው አዳዲስ የቴክኖሎጂ አሠራሮችን በመጠቀም በመሆኑ ነው። ከፍጥነት ባሻገር የጥራት ደረጃቸውን የጠበቁ ቤቶችን በተያዘው የማስረከቢያ ጊዜ ውስጥ ለመጨረስ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተሠራ ነው። እንደ ኢንጂነር ታምራት ገለጻ የግንባታ ስርገት መከላከያ፣ የመብራትና የውሃ ዝርጋታዎች ከሕንጻው ግንባታ ጋር ጎን ለጎን እየተከናወኑ በመሆናቸው ሕንጻዎቹ ሲጠናቀቁ ለነዋሪዎች ምቹና ደረጃቸውን የጠበቁ እንዲሆኑ ያስችላሉ።

ዘመናዊነትና ምቾት በአንድ ላይ

ጉዟችንን ቀጥለን ወደ ቱሉ ዲምቱ ስናቀና ደግሞ ሌላ ተስፋ ሰጪ ሥራ እዚህም እየተከናወነ ይገኛል። እነዚህ ሕንጻዎች የነዋሪዎችን የመኪና ማቆሚያ ችግር ግምት ውስጥ በማስገባት እያንዳንዳቸው ባለ ሁለት ወለል የመኪና ማቆሚያ እንዲኖራቸው ተደርገው እየተገነቡ ነው። በኮርፖሬሽኑ የደቡብ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ እና የቱሉ ዲምቱ ሳይት አስተባባሪ ኢንጂነር ኪያ በሬቻ የሚመሩት እያንዳንዳቸው 11 ወለል ያላቸው 10 ሕንጻዎች ግንባታ በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል።

የ24 ሰዓት ርብርብ ለ9 ወራት ግብ

ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ዝም ብሎ የሚከናወን ሳይሆን ግልጽ የሆነ የጊዜ ገደብ ተቀምጦለት ነው። ፕሮጀክቱ በ9 ወራት ውስጥ ተጠናቆ ለነዋሪዎች እንዲተላለፍ የከተማ አስተዳደሩ መመሪያ ሰጥቷል። ለዚህም ስኬት ሲባል የግንባታ ሥራው ያለምንም እረፍት በሽፍት ሥራ እየተከናወነ ይገኛል – በቀን 24 ሰዓት፥ በሳምንት ደግሞ ለ7 ቀናት።

በዚህ ዓመት ብቻ እስከ 200 የሚደርሱ ሕንጻዎች ተገንብተው ይጠናቀቃሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ለዚህ ደግሞ መንግስት ለተቋራጮችና ለአማካሪ ድርጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑ ዋናው ሞተር መሆን ችሏል።

በግንባታ ሳይቶቹ ላይ ቀን ከሌሊት የሚንጎማለሉት የግንባታ ማሽኖች እና የግንባታ ቁሳቁሶች ተራ ብረትና ሲሚንቶ አይደሉም፤ በሽህ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች የቤት ባለቤት የመሆን ሕልም እውን የሚሆንባቸው ተስፋዎች እንጂ። ፍጥነት፣ ጥራትና ቴክኖሎጂ ተደምረው የከተማዋን ነዋሪዎች የቤት ፍላጎት በዘላቂነት ለመቅረፍ በመንገድ ላይ ናቸው።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review