በአዲስ አበባ የተጀመሩት ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው

You are currently viewing በአዲስ አበባ የተጀመሩት ቤቶች ግንባታ እየተፋጠነ ነው

AMN – ታኅሣሥ 21/2018 ዓ.ም.

በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የመኖሪያ ቤት ፍላጎት ለማርካት በዘንድሮው ዓመት ብቻ 100 ሺህ ቤቶችን ለመገንባት ታቅዶ በ18 ሳይቶች ላይ ሥራው በሙሉ አቅም እየተከናወነ እንደሚገኝ የከተማዋ የቤቶች ልማት አስተዳደር ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ ተናግረዋል።

የግንባታ ሒደቱን ለማፋጠንና ወጪን ለመቀነስ አዳዲስ የቴክኖሎጂ ግብዓቶች ጥቅም ላይ የዋሉ ሲሆን ግንባታው በመንግስት ብቻ ሳይወሰን በሪል ስቴት አልሚዎች፣ በግል እንዲሁም በማኅበር ተደራጅተው የሚሰሩትንም በመጋበዝ ጭምር በአምስት የተለያዩ አማራጮች እየተተገበረ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም የጀርመን ሳይት ላይ የነበረውን ተሞክሮ በመውሰድ ሁለት ብሎኮችን በ”ዊንግ” የማገናኘት ስራ የተከናወነ ሲሆን ይህም የሊፍት ወጪን ከመቀነሱም በላይ የመሬት ብክነትን በማስቀረት በአነስተኛ ቦታ ላይ በርካታ ቤቶችን ለመገንባት አስችሏል።

25 ሺህ ቤቶች በሚገነባበት የገላን ጉራ ሳይት እየተካሄደ ያለው ግንባታ የቴክኖሎጂውን ውጤታማነት በተግባር ያሳየ ሆኗል።

በአሁኑ ወቅት ለሙከራ እየተገነቡ ያሉ ብሎኮች አስገራሚ ፍጥነት እያሳዩ ሲሆን፣ በ52 ቀናት ውስጥ ብቻ 10ኛ ፎቅ ላይ መድረስ መቻሉ የግንባታውን ቅልጥፍና ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል ብለዋል ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የቢሮው ኃላፊ ወ/ሮ ቅድስት ወልደ ጊዮርጊስ።

ከተማዋን “ስማርት” የማድረግ ራዕይን ሰንቀው እየተገነቡ ያሉት እነዚህ መንደሮች፣ መኖሪያ ቤት ከመሆን ባለፈ የተሟላ መሠረተ ልማት ይኖራቸዋል። በአረንጓዴ ልማት የታጀቡ፣ ለህፃናት መጫወቻ፣ ለአዛውንቶች መዝናኛና ለወጣቶች የስፖርት ማዘውተሪያዎችን ያካተቱ ዘመናዊ መንደሮች ሆነው ነው እየተገነቡ ያሉት።

ይህ ሰፊ የግንባታ እንቅስቃሴ ለከተማዋ ነዋሪዎች መጠለያ ከመፍጠር ባለፈ፣ ሰፊ የሥራ ዕድልን ይዞ መጥቷል። በገላን ጉራ ሳይት ብቻ ሳይወሰን በሁሉም 18 ሳይቶች ግንባታው “ከላይ ስኬሌተኑ ሲቆም ከታች ግንባታው አብሮ የሚሄድበትን” አዲስ የቴክኖሎጂ ሀሳብ በመጠቀም በጥራትና በፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል። ይህም በዘንድሮው ዓመት የታቀዱትን 100 ሺህ ቤቶች ለተጠቃሚዎች ለማድረስ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ትልቅ እምነት ጥሏል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review