በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሴቶችን ያከበረች ከተማ አዲስ አበባ

AMN- ነሐሴ 6/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተገነቡ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ሁሉ የተለየና የላቀ ትርጉም ያለው ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በአስቸጋሪና በምስቅልቅል ሁኔታ ውስጥ የነበሩ ሴችን ህይወት የቀየረ ለብዙዎች የመንፈስ እርካታን ያጎናፀፈ ዘመን ተሻጋሪ ስራ ነው፡፡

ማዕከሉ ከዚህ ቀደም ትኩረት የተነፈጋቸው እና በጎዳና ላይ በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ይኖሩ የነበሩና ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ የነበሩ ሴቶችን ከነበሩበት አሰቃቂ ህይወት በማላቀቅ በመንከባከብና መጠለያ በመሆን ህይወታቸው እንዲቀየርና ገቢ እንዲያገኙ ብሎም እራሳቸውን እንዲችሉ በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጾ እያበረከተ ይገኛል፡፡

በመዲናችን አቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚገኘውና በከተማ አስተዳደሩ መልካም እሳቤ የተገነባው የነገዋ የሴቶች ተሀድሶ እና ክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በአንድ ጊዜ እስከ 2 ሺህ በዓመት ደግሞ እስከ 10 ሺህ የሚደርሱ ሴቶችን የመቀበል አቅም አለው፡፡

ይህ ግዙፍና ለብዙዎች የመንፈስ እርካታን ያጎናፀፈ ፕሮጀክት በአስቸጋሪ ህይወት ይኖሩ የነበሩ ሴቶችን ከነበረባቸው ሁለንተናዊ ችግር በማላቀቅ ኑሯቸውን በማሻሻል የሥነ ልቦና ድጋፍ እና የጤና እንክብካቤ እንዲያገኙ በማድረግ በስነ-ውበት፣ በፋሽንና ጨርቃ ጨርቅ፣ በምግብ ዝግጅት እንዲሁም በሌሎች 18 የሙያ ዘርፎች የተሟላ ዕውቀት እንዲያገኙ በማድረግ በቀጥታ ወደ ስራ እንዲገቡ እያደረገ ይገኛል፡፡

በአጠቃላይ ከተመሠረተ ጀምሮ በድምሩ 3 ሺህ 258 ሰልጣኞችን በማብቃት ወደ ስራው ዓለም እንዲቀላቀሉ በማድረግ ህይወታቸውን በተሻለ መንገድ እንዲመሩና ለሌሎችም አርዓያ እንዲሆኑ በማድረግ ላይ ይገኛል።

ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል በከተማ አስተዳደሩ የሚተገበሩ ግዙፍ ፕሮጀክቶች የሰው ህይወት ላይ መሰረት ያደረጉ የብዙዎችን እንባ ያበሱ እንዲሁም ታሪክን በደማቁ የፃፉ ስለመሆናቸው ይህ ታላቅ ስራ ህያው ምስክር መሆኑን የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ መረጃ ያመለክታል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review