ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓል ማጠቃለያ ላይ ተገኝተው፣ ከምሁራን ለተነሱላቸው ጥያቄዎች ሰፊ ምላሽ እና ማብራርያ ሰጥተዋል።
በሀገራዊ ጉዳይ ምሁራንን ማሳተፍ የፍቃድ ጉዳይ ሳይሆን የመንግስታችን የፖሊሲ አቅጣጫ መሆኑን በስልጠናዎች፣ ውይይቶችና እሳቤዎች ስለተገለጸ ምሁራን መንግስት የሚሄድበትን መንገድ አገላብጠው በማዬት ችግር ካለ እንዲታረም ሀሳብ እንዲያቀርቡ በሩ ክፍት መሆኑን ገልጸዋል።
ከዚህ በፊት በኢትዮጵያ የመንግሥታት ታሪክ ውስጥ የኢኮኖሚ ሪፎርሞችንና አሳቤዎችን በጽሑፍ በማውጣት፣ ምሁራን እንዲተቹ፣ እንዲወቅሱና እንዲያርሙ እራሱን ዝግጁ ያደረገ መንግሥት እንዳልነበረ ገልጸዋል።
“ዋናው የምሁራን ሚና ከራስ ጋር መታረቅ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሁር ማለት አዳዲስ እውቀትን ተቀብሎ ሁሌም ለመማር ዝግጁ የሆነ ሰው መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ለዚህም ተግባራዊ ምላሽ ይሆን ዘንድ፣ ወጣት የዩኒቨርሲቲ ምሁራን ትላልቅ የሥራ ኃላፊነት ላይ እንዲቀመጡና የረዥም ጊዜ ልምድ ያላቸው ሰዎች ደግሞ ቦታውን ለትውልዱ እንዲለቁ እየተሠራ መሆኑንና ወደፊትም እንደሚቀጥል ጠቁመዋል።
የትምህርትን ጥራት ሽግግር እንዲረጋገጥ ዩኒቨርሲቲዎች ሀሳብ ፈጣሪና ለዘመኑ የሚመጥኑ መሆን እንዳለባቸውም አሳስበዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ከመንግስት ጥገኝነት ተላቀው እራሳቸውን ችለው መቆም እንዳለባቸው የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ሂደት ከአንጋፋው አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መጀመሩንና ወደ ሌሎችም እንደሚስፋፋ ተናግረዋል።
“መካነ-ትምህርት” አንዱ የአመራር አካል በመሆኑ፣ እሱ ከጎደለ የምናስበውን ብልጽግና ማሳካት አይቻልም” በማለት የምሁራንን ሚና አስፈላጊነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ