ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሩ

You are currently viewing ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምሩ

AMN ጥር 02/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ግንባታ ሥራን የመሠረት ድንጋይ በማስቀመጥ በዛሬው ዕለት በይፋ አስጀምረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንኑ አስመልክቶ በማኅበራዊ ትሥሥር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት፣ “የኢትዮጵያን ፈጣን የአየር ትራንስፖርት ዕድገት እና እየሰፋ የመጣውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዓለም አቀፍ ትሥሥር ዘላቂ ለማድረግ ወደ 25 ሚሊዮን የሚጠጉ መንገደኞችን በዓመት የማስተናገድ አቅሙ ላይ ከደረሰው ከአዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተጨማሪ አዲስ ሜጋ ጣቢያ እየለማ ይገኛል” ብለዋል።

ይህ የተለያዩ አውሮፕላን ማረፊያዎችን የመገንባት ስትራቴጂ ኢትዮጵያን የወደፊቷ የአፍሪካ ግንባር ቀደም የአየር ትራንስፖርት በር የማድረግ ዓላማን ያነገበ መሆኑን ነው የገለጹት።

የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በአፍሪካ ታሪክ ትልቁ የአየር ትራንስፖርት መሠረተ ልማት ፕሮጀክት እንደሚሆንም ጠቁመዋል።

ይህም ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የኢንደስትሪ ማስፋፊያ አጀንዳ እና የረጅም ዘመን የአቪየሽን ስትራቴጂ ጋር የተናበበ ነው።

ፕሮጀክቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድን አለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያጠናክራል ሲሉ ገልጸዋል።

በAfCFTA ማህቀፍ የአፍሪካን የማገናኘት አቅም ይጨምራል። የንግድ እና ቱሪዝም ኮሪደሮችን ያሰፋል። ኢትዮጵያንም ቀዳሚ የበይነአኅጉር ማዕከል ያደርጋታል።

ከአዲስ አበባ ደቡብ ምስራቅ 40 ኪሎሜትር አካባቢ የምትገኘውና 1910 ሜትር ከፍታ ያላት ቢሾፍቱ ለአውሮፕላኖች ሥራ የተመቸ ከባቢ ያላት ሲሆን መዳረሻቸውን ኢትዮጵያ ላደረጉም ሆነ ለትራንዚት መንገደኞች ብቁ ሁኔታ ያላት ናት።

ለመዲናችን ያላት ቅርበት ከነባሩ የአየር ትራንስፖርት ምኅዳር ጋር በቀላሉ የተዋሃደ አሠራር እንዲኖር ምቹ ሁኔታ ይፈጥራል ብለዋል።

የመጀመሪያው ምዕራፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ሥራ በአመት 60 ሚሊዮን ተጓዦችን የሚያስተናግድ ሲሆን ሲጠናቀቅም አፍሪካን ከአለም ቀዳሚ የአየር ትራንስፖርት መነኻሪያዎች አንዷ የሚያደርጋትን በአመት 110 ሚሊዮን መንገደኞችን የማስተናገድ አቅም ላይ ይደርሳል ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review