ማቀዝቀዣ (ፍሪጅ) ምግብ ትኩስነቱን እንደያዘ ሳይበላሽ ለማቆየት የሚያገለግል ዘመናዊ የምግብ ማስቀመጫ ዋና መሳሪያ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡
ዝቅተኛ የሙቀት መጠን፣ ምግቦች ጥራታቸውን ጠብቀው እንዲቆዩ እንደሚያደርግ የተደረጉ ሙከራዎችም ያረጋግጣሉ፡፡
ነገር ግን ሁሉም ምግቦች ማቀዝቀዣ ውስጥ እንዲቀመጡ ይመከራል ማለት ሳይሆን፣ ከተፈጥሯዊ ባህሪያቸው የተነሳ አንዳንድ ምግቦች ማቀዝቀዣ ውስጥ ሲቀመጡ ቅርፃቸውን፣ ጣዕማቸውን እና የምግብነት ይዘታቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ የታይምስ ኦፍ ኢንዲያ እና ሌሎች የጤና መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በእነዚህ የጤና መረጃዎች መሠረትም፣ በፍሪጅ ውስጥ ፈጽሞ መቀመጥ ከሌለባቸው ምግቦች መካከል የተወሰኑትን ከነምክንያቶቻቸው እንደሚከተለው እንመለከታለን፡-
ቲማቲም (Tomatoes): በፍሪጅ ውስጥ ሲቀመጥ የቲማቲም ተፈጥሯዊ ጣዕምና መዓዛ ይጠፋል። ቅዝቃዜው በውስጡ ያሉትን ኢንዛይሞች ስለሚጎዳ ቲማቲሙ እንዲለሰልስና እንዲላላ (mushy) ያደርገዋል።
ድንች (Potatoes): ቅዝቃዜው በድንች ውስጥ ያለውን ስታርች (starch) ወደ ስኳር ይቀይረዋል። ይህ ደግሞ ድንቹ ሲበስል ጣዕሙ እንዲቀየርና እንዲጠቁር ያደርጋል። በተጨማሪም ለጤና ጎጂ የሆኑ ኬሚካሎች እንዲፈጠሩ ሊያደርግ ይችላል።

ቀይ ሽንኩርት (Onions): ሽንኩርት በፍሪጅ ውስጥ ባለው እርጥበት ምክንያት ቶሎ እንዲበሰብስና ሻጋታ እንዲይዘው ያደርጋል። ሽንኩርት አየር በሚያገኝበት ደረቅ ቦታ መቀመጥ አለበት።
ነጭ ሽንኩርት (Garlic): በፍሪጅ ውስጥ ሲቀመጥ የመብቀል (sprout) እድሉ ከፍተኛ ነው። እንዲሁም እንዲለሰልስና እንዲሻግት ያደርገዋል።
ዳቦ (Bread): ብዙ ሰው ዳቦ ቶሎ እንዳይበላሽ ፍሪጅ ውስጥ ያደርጋል፤ ነገር ግን ቅዝቃዜው ዳቦው ቶሎ እንዲደርቅና ጣዕሙን እንዲያጣ ያደርገዋል።

በሶቢላ (Basil): ይህ ቅመም (ቅጠል) በፍሪጅ ውስጥ ሲቀመጥ ቶሎ ይጠወልጋል እንዲሁም በዙሪያው ያሉትን ሌሎች ምግቦች ሽታ የመምጠጥ ባሕርይ አለው። በውኃ የተሞላ ብርጭቆ ውስጥ አድርጎ ውጭ ማስቀመጥ ይመረጣል።
ማር (Honey): ማር በፍሪጅ ውስጥ ሲቀመጥ እንዲረጋና እንዲጠነክር ያደርገዋል። ማር ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽ ስለሚቆይ በቤት ሙቀት ውስጥ ማስቀመጥ በቂ መሆኑን መረጃዎቹ ይጠቁማሉ።
በመሆኑም እነዚህ ምግቦች በፍሪጅ ውስጥ ከመቀመጥ ይልቅ አየር በሚያገኙበትና ደረቅ በሆነ የክፍል ሙቀት ውስጥ ቢቀመጡ ለረጅም ጊዜ ትኩስነታቸውንና ጣዕማቸውን ጠብቀው መቆየት ይችላሉ።
በታምራት ቢሻው