የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት የወሎ የብልጽግና ተስፋ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

You are currently viewing የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት የወሎ የብልጽግና ተስፋ ነው – ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

AMN – ሚያዝያ 08/2018 ዓ.ም

የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ጸጋን የመለየት፣ የማልማትና ወደ ሀብት የመቀየር ማሳያ እና የወሎ የብልጽግና ተስፋ ነው ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ተናገሩ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሣሽነት እና በ”ገበታ ለትውልድ” መርሐ ግብር የተገነባውን የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ሥራ አስጀምረዋል፡፡

ዛሬ በታሪካዊቷ የሐይቅ ከተማ ከማኅበረሰቡና ከአፋር ወንድሞቻችን ጋር በአንድነት ተገኝተን፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አነሣሽነት እና በ”ገበታ ለትውልድ” መርሐ ግብር የተገነባውን የሎጎ ሐይቅ ሪዞርት ሥራ ለማስጀመር በመቻላችን ታላቅ ደስታ ይሰማኛል ብለዋል። ወሎ ማለት ኅብር ነው። ዛሬም በዚህ በዓል ላይ ከአፋር ወንድሞቻችን ጋር መገኘታችን ይህንኑ ውበታችንን የሚገልጥ ነው።

ይህ ፕሮጀክት ከግንባታው ጅማሮ እስከ ፍጻሜው የ”መደመር” ዕሳቤ በተግባር የታየበት፣ የመንግሥት ሐሳብ፣ የባለ ሀብቱ ታታሪነት እና የሕዝቡ ትጋት የተሰባጠረበት ድንቅ ውጤት ነው ሲሉ ገልጸዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ፤ ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ሌት ተቀን ለጠበቁት የመከላከያ፣ የፖሊስ እና የሚሊሻ አባላት፣ እንዲሁም ለአካባቢው አመራርና ሕዝብ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

ባለሀብቱ አቶ በላይነህ ክንዴ ሪዞርቱን ውብ አድርገው ከመገንባት ባለፈ፣ ጫትን በምርጥ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያ በመተካት ለውጥ በተግባር እንደሚመጣ አሳይተዋል። ለሐይቅ ከተማ የገነቡት ትምህርት ቤትም ለትውልድ የሚተርፍ ተግባር ነው ብለዋል።

ዛሬ ያየነው ልማት የሰላም ውጤት ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ወጣቶች ሰላማቸውን አጥብቀው እንዲጠብቁ አደራ ብለዋል።

በአንድነት እና በትጋት ከሠራን፣ ይህ ቀጣና የዕድገትና ብልጽግና መዳረሻ መሆኑ አይቀሬ ነው! ሲሉም በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው አስፍረዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review