በፒያሳ እና አካባቢዉ የተገነቡ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ለአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ አላብሰዋታል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

You are currently viewing በፒያሳ እና አካባቢዉ የተገነቡ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ለአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ አላብሰዋታል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ

AMN – ጥር 4/2018 ዓ/ም

በፒያሳ እና አካባቢዉ የተገነቡ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሥራዎች ለአዲስ አበባ አዲስ ገጽታ አላብሰዋታል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለመዲናዋ አዲስ ገጽታ ያላበሱትን በፒያሳና አራዳ አካባቢ የተገነቡ የወንዝ ዳርቻ ልማቶችን ተዘዋዉረዉ በመጎብኘት ገለጻ አድርገዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት፤ አራዳ ፓርክና ፒያሳ አዲስ አበባን እንደ አዲስ በሚያሳይ ከፍታ በአጭር ጊዜ ተገንብተዋል።

ይህ ለውጥ የከተማዋን ውበት ብቻ ሳይሆን የማንነት መገለጫ ጭምር ሆኗል ነው ያሉት።

በከተማዋ የለሙ የወንዝ ዳርቻዎች የወንዙን ተፈጥሯዊ ፍሰት ሳይገቱ፣ ከሥነ-ምህዳሩ ጋር በተስማማ መልኩ ለአይን በሚማርክ ውበት መገንባታቸውን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል በአካባቢው የተገነባ ህንጻ እምብዛም አለመኖሩን አስታውሰው፤ አሁን ላይ አዳዲስ ህንጻዎች ተገንብተው ለከተማዋ ተጨማሪ ድምቀት መሆናቸውን ተናግረዋል።

ህንጻዎቹ ከወንዞችና ከተፈጥሮ ጋር ተስማምተው ሲታዩ መንፈስን ያድሳሉ ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ከዚህ የተነሳ ፕሮጀክቶቹ በይፋ ሳይከፈቱ ነዋሪዎች እየተዝናኑበት እንደሆነ ገልፀዋል።

እነዚህ ፕሮጀክቶች ለነዋሪዎች የመንፈስ እርካታ ከመፍጠራቸው ባሻገር አዲስ አበባን የዘመናዊነት ማዕከል አድርገዋታል።

አካባቢውን የሚያሳምሩና ለነዋሪዎች ምቹ የሆኑ አዳዲስ መንገዶች መገንባታቸውም ተዳማሪ ድምቀት መሆናቸውን ገልጸዋል ።

በአጥር ተከልሎ የመኖር አሮጌ ባህል ቀርቶ፣ የጋራ መጠቀሚያ ሥፍራዎችን በማስፋፋት ዘመናዊ የከተማ አኗኗር እንዲስፋፋም ተደርጓል።

ይህ ስኬት የመንግስት፣ የግሉ ዘርፍ እና የአልሚዎች የጋራ ጥረት ውጤት መሆኑን ከንቲባ አዳነች ገልጸው ለተሳትፎቸውም ምስጋና አቅርበዋል።

በበረከት ጌታቸዉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review