ወጣቶችን ለስደት እየዳረገ ያለው ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን…

You are currently viewing ወጣቶችን ለስደት እየዳረገ ያለው ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን…

AMN- ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን የትግራይ ክልል ወጣቶችን ለስደት እና እንግልት እየዳረገ ነው፡፡

የትግራይ ክልል ህዝብ ሰላም በማግኘት ሰርቶ መለወጥና የልማት ተጠቃሚ መሆን ሲገባው በሕገ-ወጡ የህወሓት ቡድን ግፍ እና አፈና እየደረሰበት ይገኛል፡፡

ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ በትግራይ ክልል ጦርነት ቆሞ ሰላም ሰፍኖ የነበረ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ስምምነቱን በመጣስ የክልሉን ህዝብ ወደ ጦርነትና መከራ ለመክተት ጥረት እያደረገ ነው፡፡

በሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን እየተፈጸመ ያለውን አፈና እና የግዳጅ ድርጊት ለማውገዝ ከሁለት ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ከተማ መስቀል አደባባይ በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ትግራይ ክልል ጦርነት ሳይሆን ልማት፣ ፍቅር እና ሰላም ነው የሚፈልገው ብለዋል፡፡

ቡድኑ ወጣቶችን ከትምህርት ቤት አስገድዶ እየወሰደ ነው ያሉት የክልሉ ተወላጆች፤ የትግራይ ክልል እናቶችን ማስለቀስ ይብቃ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቡድኑን እኩይ ተግባር ማውገዝ እንዳለበት በመግለጽ በክልሉ ሕገ- ወጥ ቡድኑ እያደረገ ያለውን አፈና እና ግፍ ሊያቆም ይገባል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በትግራይ ክልል ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ወጣቶችን እያፈነ ለወታደራዊ ፍጆታ የማዋል ተግባሩን ማቆም አለበትም ነው ያሉት፡፡

እናቶች ልጆቻቸውን ለጦርነት አንሰጥም በማለት ሕገ-ወጥ ቡድኑን እየተቃወሙ ሲሆን በቡድኑ ምክንያት ጦርነትን የጠሉ ወጣቶች የትውልድ አካባቢያቸውን ለቀዋል፡፡

በትናንትናው ጥፋት የእናቶች እንባ ሳይሻር እንዲሁም ሃዘናቸው ሳይደርቅ በአሁኑ ጊዜም ወጣቶች በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ጦርነት እየተላኩ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ሕገ-ወጡ የሕወሓት ቡድን ዳግም ጦርነትን በመምረጥ ሴቶች፣ ህጻናት እንዲሁም ወጣቶችን በአስገዳጅ ሁኔታ ወደ ጦርነት እየማገደ ይገኛል፡፡

ቡድኑ ወጣቶችን በማፈን ከሚፈፅመው ግፍ በተጨማሪ የክልሉ ነዋሪዎች የእለት ተእለት ሥራቸውን በአግባቡ እንዳያከናውኑ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡

የሻምበል ምህረት

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review