AMN – ጥር 05 ቀን 2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ የበጎ ፈቃድና የህብረተሰብ ተሳትፎ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የተገነቡ 4 ሺህ 690 የመኖሪያ ቤቶች ለአቅመ ደካሞች ማስተላለፍ መቻሉን ገለጸ።
ኮሚሽኑ በሰው ተኮር ተግባራት በመኖሪያ ቤት ግንባታ፣ በማዕድ ማጋራት፣ በጤና ዘርፍ አገልግሎትና በሌሎች የበጐ ፈቃደኞች በተሰሩ ሥራዎች አመርቂ ውጤቶችን ማስመዝገቡን አስታውቋል።
የኮሚሽኑ ምክትል ኮሚሽነር ወይዘሮ አስራት ንጉሴ ከኤ ኤም ኤን 24/7 ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ከተማ አስተዳደሩ ባለፉት የለዉጥ ዓመታት በርካታ ሰው ተኮር ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል ብለዋል።
ለአብነትም ባለፉት ስድስት ወራት በክረምት በጎ ፈቃድ 15 መርሃ ግብሮች ፣ እንዲሁም ከጥቅምት 1 ጀምሮ በበጋ 13 መርሃ ግብሮች ላይ ትኩረት በማድረግ ወደ ሥራ መገባቱን ጠቁመዋል።
ቀደም ሲል በነበሩት ዓመታት ትኩረቱ በቤት ግንባታና እድሳት ላይ የነበረ ቢሆንም፤ አሁን ላይ ግን ከተማዋ እያደገች ከመምጣቷ ጋር ተያይዞ ያረጁ ቤቶችን ሙሉ በሙሉ በማፍረስ በአዲስ መልክ በመገንባት የዜጎችን ኑሮ ምቹ የማድረግ ስልትን እየተከተለ መሆኑን ምክትል ኮሚሽነሯ ገልጸዋል።
በጐፈቃደኛ ባለሀብቶችን በማስተባበር በገና በዓል ብቻ 381 ቤቶች ከነሙሉ የቤት እቃዎቻቸው በከንቲባ አዳነች አቤቤ አማካኝነት ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውን ተናግረዋል።
የጎደሉ ጓዳዎችን ለመሙላትና ያዘመሙ ጎጆዎችን ለማቅናት በተደረገው ጥረትም ለገና በዓል ከ300 ሺህ በላይ ለሀገር ባለውለታዎች፣ ለአካል ጉዳተኞችና በአልጋ ቁራኛ ለሆኑ ዜጎች ቅድሚያ ተሰጥቶ ድጋፍ ተደርጓል።
ኮሚሽኑ ከቤት ግንባታ ባሻገር በበጎ ፈቃደ አገልግሎት ላይ መጠነ ሰፊ ሥራዎችን ያከናወነ ሲሆን፤ ከ60 ሺህ በላይ ዩኒት ደም በበጎ ፈቃደኛ ወጣቶች በመለገሱ የብዙዎችን ህይወት ማዳን መቻሉንምክትል ኮምሽነሯ ገልፀዋል።
ከ241 ሺህ በላይ አቅም የሌላቸው ዜጎች በመንግስትና በግል የጤና ተቋማት አማካኝነት ከተመላላሽ እስከ ተኝቶ ህክምና ድጋፍ እንዲያገኙ ተደርጓል።
በትራፊክ ፍሰት በሚጨናነቁ 106 አካባቢዎች 10 ሺህ የሚጠጉ በጎ ፈቃደኛ ወጣቶች የትራፊክ ፍሰቱን በማሳለጥ በነፃ እያገለገሉ ይገኛሉ።
“ሰው ለመርዳት ሰው መሆን ብቻ በቂ ነው” በሚል መሪ ቃል ኮሚሽኑ የሚረዱና የሚደገፉ ዜጎችን በማገናኘት አመርቂ ውጤት ማግኘቱን ወ/ሮ አስራት ገልፀዋል፡፡
የኢትዮጵያዊ የመረዳዳትና የመተጋገዝ እሴትን ተቋማዊ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሯ፤ ዜጎች ማህበራዊ ኃላፊነታቸውን በመወጣት አሁን ላይ የሚስተዋሉ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮችን በጋራ ለመቅረፍ መተባበር እንደሚገባ ምክትል ኮሚሽነሯ ጥሪ አስተላልፈዋል::
በበረከት ጌታቸው