የዓለም አቀፉ ታዋቂ የሶሻል ሚዲያ ተጽዕኖ ፈጣሪ IShowSpeed የኢትዮጵያ ቆይታ፤ በመላው ዓለም የሚሊዮኖች ዓይኖች ወደ አዲስ አበባ እንዲሳቡ ያደረገ ስኬታማ መርሃ-ግብር ነበር ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጿል፡፡
ከንቲባ አዳነች በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልእክት፤ ይህ ጉብኝት ከተማችን ያላትን የቆየና የከበረ የእንግዳ ተቀባይነት ባህል፣ የከተማችንን ፅዳትና ውበት፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን ትክክለኛ ገፅታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለማስተዋወቅ ትልቅ ዕድል ፈጥሯል። ኩነቱ እስካሁንም መነጋገሪያነቱ የቀጠለ ሲሆን፣ ወደፊትም ብዙዎችን ወደ ሀገራችን ይስባል ብለን እናምናለን ብለዋል።

ይህንን ኩነት በብቃት ላከናወናችሁ ሀገር ወዳድ፣ ጎበዝ እና ተፅዕኖ ፈጣሪ ወጣቶች፣ የግል እንዲሁም የፌደራልና የአዲስ አበባ መንግስታዊ ተቋማት ልባዊ ምስጋና ይገባችኋልም ብለዋል።
በተለይም የቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን፣ የአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ቢሮ፣ ይሳቃል ኢንተርቴይመንት እና ሌሎችም በቅንጅት የሠራችሁ አካላት በሙሉ፤ ያሳያችሁት የላቀ የቅንጅት አቅም እና የሀገር ፍቅር ስሜት ‘ይበል’ ያሰኛል ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።