በአዲስ አበባ ከተማ እየታየ ያለው ሰፊ የገጽታ ለውጥ፣ ከተማዋ ለዲፕሎማሲና ለዓለም አቀፍ ግንኙነት ያላትን ተመራጭነት በከፍተኛ ሁኔታ እያሳደገው መሆኑን የፖለቲካ እና የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተመራማሪው አቶ እያሱ ግዛው ገለጹ።
ተመራማሪው ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ አዲስ አበባን የዲፕሎማሲ መዳረሻና ተመራጭ ከተማ ያደረጓት ታሪካዊ፣ ፖለቲካዊና ተፈጥሮአዊ ምክንያቶች ቢኖሩም፤ በአሁኑ ወቅት እየተከናወነ ያለው የመሠረተ ልማት መስፋፋትና የገጽታ ለውጥ ከተማዋን ለዲፕሎማሲ ሥራ ይበልጥ ሳቢና ማራኪ እያደረጋት ይገኛል።
ኢትዮጵያ የረጅም ጊዜ የመንግሥትነት ታሪክ ያላት ሀገር መሆኗ ለዲፕሎማሲው ስኬት ትልቅ መሠረት የጣለ መሆኑን ተመራማሪው ገልፀው፤ በተለይም ከአድዋ ድል በኋላ በርካታ የምዕራባውያን ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት ለመጀመር ኤምባሲዎቻቸውን በአዲስ አበባ መክፈታቸው ከተማዋን የዲፕሎማሲ ማዕከል አድርጓታል ብለዋል።
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ሕብረት) ሲመሰረት ኢትዮጵያ የተጫወተችው ከፍተኛ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ሚና፣ አዲስ አበባ የአህጉሪቱ የዲፕሎማሲ መዲና እንድትሆን አስችሏታልም ብለዋል።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ በመደናዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕሴቶችን የሚጨምሩ ሁለንተናዊ ስራዎች መዲናዋን የስበት ማዕከልነት እንዲጨምርም አስችሏል ብለዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ አስተማማኝ የሰላምና ጸጥታ ሁኔታ መኖሩ፣የመሠረተ ልማት መስፋፋትና ምቹ የአየር ንብረት መኖሩ ለኮንፈረንስ ቱሪዝምና ለዲፕሎማቶች ቆይታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቅሰዋል።
ተመራማሪው አቶ እያሱ ግዛው አክለውም፣ የሀገሪቱ የውጭ ግንኙነት እና የዲፕሎማሲ ባህሪ ሳይለዋወጥ ለረጅም ጊዜ መቆየቱ ለዘርፉ መረጋጋትና እድገት የራሱ የሆነ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው ገልጸዋል።
በበረከት ጌታቸው