በአዲስ ገጽታ አዲስ ትውስታ

You are currently viewing በአዲስ ገጽታ አዲስ ትውስታ

“ባለፈው ዓመት ለጥምቀት በርካታ ፎቶዎችን አንስቻለሁ፤ ዘንድሮም ብዙ ፎቶ አነሳለሁ ብዬ እጠብቃለሁ”
የፎቶ ግራፍ ባለሙያው ሙሉቀን ባዬ

ጥምቀት በኢትዮጵያ ከኃይማኖታዊ ስነ- ስርዓትነቱ ባለፈ፣ የጥበብ፣ የባህል እና የሕዝብ አንድነት በታላቅ ድምቀት የሚታይበት ልዩ አጋጣሚ ነው። በየዓመቱ ጥር 11 ቀን የሚከበረው ይህ በዓል፣ ኢትዮጵያን በዓለም አደባባይ በኩራት ከሚያቆሟት የማይዳሰሱ ቅርሶች መካከል አንዱ ነው።

ታቦታት ከየአቢያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው በታላቅ ዝማሬና እልልታ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ (ማደሪያቸው) ሲያቀኑ፣ መላው የእምነቱ ተከታይ የሆነው ህዝብ አጅቦአቸው ይወጣል። የካህናቱ ያሬዳዊ ወረብ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ተማሪዎች ዝማሬ እና የፈረሰኞች ግልቢያ (በገጠር አካባቢ) መንገዱን ሁሉ በደስታ ይሞላዋል። ይህ በዓልና ታቦታትን አጅቦ የሚደረገው ጉዞ የምድራዊ ደስታና የመንፈሳዊ እርካታ ድብልቅ ስሜት የሚፈጥር ልዩ ትርኢት ነው።

በዚህ ምክንያት ጥምቀት በብዙዎች ልብ ውስጥ የማይረሳ የልጅነት አሻራ ጥሎ የሚያልፍ በዓል ነው ማለት ይቻላል። ከበዓሉ መንፈሳዊነት ጎን ለጎን፣ ማኅበራዊ ገጽታውና ሰዎች በበዓሉ ወቅት ያሳለፉት የልጅነትም ሆነ አዋቂነት ታሪክ ሁሌም በናፍቆት ይታወሳል።

“ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚለው ብሂል፣ በዓሉን በአዲስነትና በንጽሕና የመቀበል ባህል መግለጫ ነው። እንዲሁም ወጣቶች ምንጣፍ ለማንጠፍ የሚያደርጉት ጥድፊያ፣ የዘማሪን ጥዑም ድምጽ እና ከባሕረ ጥምቀቱ ጸበል ለመረጨት የሚደረገው ግብግብ የበዓሉን ተናፋቂነት በግልፅ የሚያመላክቱ ናቸው።

በሀገራችን ቴክኖሎጂ እየተስፋፋ ሲመጣ የጥምቀት አከባበር ትዝታን ከአዕምሮ ትውስታ በተጨማሪ በፎቶ ማስቀረት ባህል ማድረግ እየተቻለ ነው። በዚህም ወደ ፎቶ ቤት በመሄድ ፎቶ መነሳት ተለመደ፡፡ በተጨማሪም ፎቶ ግራፍ አንሺዎች ራሳቸው የጥምቀት በዓል ላይ በመገኘት ማንሳት ጀመሩ፡፡

ወይዘሮ ሰላማዊት ገብረአምላክ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለጹት፤ በድሮ ጊዜ ፎቶ ግራፍ መነሳት እንደ ዛሬው ቀላል አልነበረም። ምክንያቱም ዘመናዊ ስልኮችና ካሜራዎች አልነበሩም፡፡ ስለዚህ ቤተሰብ አዲስ ልብሱን ለብሶ ወደ ፎቶ ቤት ይሄዳል። እዚያም በተለያዩ መልክዓ-ምድሮች (ለምሳሌ የተራራ ወይም የፏፏቴ ምስል) በተሳሉ መጋረጃዎች ፊት ለፊት ቆመው ይነሳሉ። ያ ፎቶ ታጥቦ እስኪመጣ ሳምንታት በትዕግስት ይጠበቃል።

“ለምሳሌ እኛ በጥምቀት ዕለት የተነሳናቸው ብዙ ፎቶዎች አሉን፡፡ ፎቶዎች ዛሬ ላይ የቤተሰብ ማስተዋሻ ናቸው” የሚሉት ወይዘሮ ሰላማዊት እንዲያውም አንዳንድ ፎቶዎችን በ2 እና 3 ኮፒ አሳጥበናቸው ነበር፡፡ ምክንያቱም አክስት፣ ዘመድ ወይም ጎረቤት የየራሱን ማስታወሻ መውሰድ ስለሚፈልግ እና ፎቶው ብዙ ሰው ጋር እንዲቀመጥ ለማድረግ ነው በማለት ያብራራሉ፡፡

በእርግጥም ወጣትነት፣ ወደ ውጭ የሄደ አልያም በሞት የተለዬ ዘመድ፣ የልጅነት አዲስ ልብስና ጫማ፣ ያኔ የነበረው የፀጉር አሠራር ሁሉ በእነዚያ ፎቶዎች ውስጥ ይቀመጣሉ። ፎቶው ሲታይ የተነሳበትን በዓል፣ ዕለት፣ ቦታ፣ በዕለቱ የነበረው ደስታና ድባብ ሁሉ በአዕምሮ ውስጥ ዳግም ውል ይላል፡፡

ዘመኑ በቴክኖሎጂ እያደገ ሲመጣ ሰዎች ፎቶ ለመነሳት ወደ ፎቶ ቤት ከመሄዳቸው በተጨማሪ ፎቶ ግራፍ አንሺዎች ራሳቸው ካሜራቸውን ይዘው ታቦቱ በሚያልፍበት መንገድ እና ባሕረ ጥምቀቱ አካባቢ ማንሳት ጀመሩ። ፎቶ፣ ፎቶ፣ ፎቶ… እያሉ ሕዝቡን እያስቆሙ የሚያነሱት ምስል፣ በዓሉን ይበልጥ ሕያው አድርጎት ቆይቷል። የእነ ወይዘሮ ሰላማዊትን ትዝታ ዛሬም ድረስ ህያው ካደረጉት ነገሮች ውስጥ አንዱ ይኸው ፎቶ ግራፍ ነው፡፡

ዘመናዊ ካሜራዎችና ስልኮች ሲመጡ እንዲሁም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ማራኪ መንገዶች ሲሰሩ ደግሞ ሰዎች ፎቶ ግራፎችን ከስቱዲዮ ወጣ ባለ መልኩ በመንገዶች፣ በመዝናኛ ስፍራዎችና በተለያዩ ፓርኮች ውስጥ መነሳት ጀመሩ፡፡ ቪዲዮ መቅረጽ ጀመሩ። ወጣት ማቲዎስ ታከለ እንደሚለው፣ የጥምቀት ከጓደኞቹ ጋር ፎቶ መነሳት ከጀመረ ዓመታት አልፈዋል፡፡ በእርግጥ አብዛኛውን ፎቶዎችን የሚነሳው በስልኩ ነው፡፡ በዚህም በተለያዩ የአዲስ አበባ ቦታዎች ታቦት ሲሸኝ የተነሷቸው ፎቶዎች በርካታ ናቸው፡፡

በዚህ ውስጥ ግን አንድ የተቀየረ ነገር አለ፤ ይሄውም የአዲስ አበባ ገጽታ መቀየር ነው፤ ይላል ወጣቱ፡፡ “የአዲስ አበባ አዲስ ውበት መላበስና በርካታ የፎቶ ግራፍ መነሻ ቦታዎች መኖራቸው ከዚህ በፊት ያልነበረ ነው፡፡ በፊት ፎቶ እንነሳ የነበረው በተወሰኑ ቦታዎች ነበር፡፡ አሁን ግን ከፈለግን ፋውንቴን አለ፡፡ ደስ የሚሉ አበባዎች የተተከሉባቸው መንገዶች አሉ። ታቦት ከሸኘን በኋላ ደግሞ ወደተለያዩ ፓርኮች ሄደን መዝናናት፣ ፎቶ መነሳት እና ቪዲዮ መቀረጽ እንችላለን” በማለት ማቲዎስ ያስረዳል፡፡

በእርግጥም የኮሪደር ልማቱ ለፎቶ ግራፍ ምቹ መሆን ለብዙ ወጣቶች የስራ እድል ፈጥሯል፡፡ ቀደም ሲል በቤት ውስጥ ስቱዲዮ ተወስነው ይሰሩ የነበሩ ባለሙያዎች አሁን ካሜራቸውን ይዘው በኮሪደር ልማት ወደተሰሩ ቦታዎች ወጥተዋል፡፡ በተለይም በበዓላትና በእረፍት ቀናት የፎቶ ግራፍ ባለሙያዎች ሰዎችን እያነሱ ወዲያውኑ ወደ ስልካቸው የሚልኩበት አሰራር እየተለመደ መጥቷል፡፡

ሙሉቀን ባዬ ፎቶ አንሺ ነው፡፡ በአንድ ፎቶ ቤት ተቀጥሮ መስራት ከጀመረ 6 ዓመታት አልፎታል፡፡ ከስቱዲዮ ባለፈ በእረፍት ቀናት፣ የጥምቀት፣ የኢሬቻና የመስቀል በዓላት ሲኖሩ በጎዳናዎችና በመዝናኛ ቦታዎች ፎቶዎችን ያነሳል፡፡

የፎቶ ግራፍ ባለሙያው በአስተያየቱ፣ “በበዓላት ሰዎች ከቤተሰቦቻቸው፣ ከጓደኞቻቸውና ከወዳጅ ዘመዶቻቸው ጋር ፎቶ ይነሳሉ፡፡ ባለፈው ዓመት ለጥምቀት በርካታ ፎቶዎችን አንስቻለሁ። ዘንድሮም ብዙ ፎቶ አነሳለሁ ብዬ እጠብቃለሁ” ይላል፡፡

“ዘመኑ የስማርት ስልክ እንደመሆኑ በርካቶች ፎቶ የሚነሱት በስልካቸው ነው፡፡ ይሁን እንጅ ቀላል የማይባል ሰው በካሜራ የመነሳት ፍላጎት አለው። በካሜራ ፎቶ መነሳት ለሚፈልጉ ወዲያውኑ አጥበን እንሰጣቸዋለን፡፡ አሊያም ያነሳነውን ፎቶ በብልቱዝና በቴሌግራም ወደ ስልካቸው እንልክላቸዋለን፡፡

የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የአዲስ አበባን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ ታቦታት በሚጓዙባቸው መንገዶች ላይ ሰፊና ምቹ የእግር መንገድ፣ ዘመናዊ መብራቶችና የከተማ ውበት ስራዎችን አካትቷል። ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ተነስተው ወደ ጥምቀተ ባሕር በሚጓዙበት ወቅት፣ ምዕመናን በነጭ ልብስ አጊጠውና በዝማሬ ታጅበው የሚያደርጉት ጉዞ በአዲሶቹ ሰፋፊ መንገዶች ላይ ሲከናወን ለዓይን የሚማርክ ገጽታን ይፈጥራል፤ ይሄ ለፎቶ ግራፍ ባለሙያ ሌላ ውበትና መልክ የሚሰጥ ትዕይንት ነው”  በማለት  የፎቶ ግራፍ ባለሙያው ሙሉቀን ያስረዳል ፡፡

በእርግጥም አዲስ አበባ አሁን ላይ ለዓይን ማራኪ ሆናለች። በተለይም በቅርቡ የተከናወነው የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት፣ ለከተማዋ ተጨማሪ ውበትን ፈጥሮላታል፡፡ ሰፋፊ የእግረኛ መንገዶች፣ በዘመናዊ ዲዛይን የተገነቡ አጥሮች፣ ማራኪ የሆኑ አበባዎች እና የሌሊት መብራቶች ከተማዋን  ልዩ ውበት አጎናጽፈዋታል፡፡ ይህ ለውጥ ደግሞ በኃይማኖታዊ በዓላት ወቅት፣ በተለይም ታቦታት ከቤተ መቅደስ ወጥተው ወደ ጥምቀተ ባሕር ሲጓዙ ወይም ወደ መንበራቸው ሲመለሱ የሚፈጥረው ድባብ ለየት ያለ ነው።

ቀደም ሲል ታቦታት በሚሸኙበት ወቅት የሚታየው ትዕይንት በጠባብ መንገዶችና በአቧራ የታጀበ ነበር። ዛሬ ግን ምዕመናን በነጭ ልብሳቸው አጊጠው፣ የቤተ ክርስቲያን መዘምራን ደግሞ በያሬዳዊ ዜማቸው እየዘመሩ በእነዚህ ውብና ንጹሕ ጎዳናዎች ላይ ሲጓዙ ማየት መንፈሳዊ ደስታን ብቻ ሳይሆን ልዩ የሥነ-ልቦና እርካታን ይሰጣል። መንገዶቹ መጽዳታቸውና መዋባቸው ምዕመኑ በነፃነት እንዲንቀሳቀስና ታቦታትን እንዲሸኝ እድል ፈጥሯል ማለት ይቻላል። ይህ በአዲስ አበባ ኮሪደሮች ላይ የሚታየው ትዕይንትና የበዓላት ፎቶ ግራፎች ለሰዎች እንደ ማስታወሻ ከማገልገሉም በተጨማሪ ለታሪክ ተመራማሪዎችና ለነገው ትውልድ ትልቅ ትርጉም አለው። ከተማዋ በምን ዓይነት ፍጥነት እየተለወጠች እንደሆነ እንዲረዳ ያደርጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ሕዝቡ ከዚህ ለውጥ ጋር እንዴት እንደተዋሃደ የሚያሳይ ህያው ምስክር የመሆን ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ታቦት እየሸኙ የሚነሱ ፎቶዎች በቤተሰብ አልበም ውስጥ ሲቀመጡ፣ ከዓመታት በኋላ ልጆች ”በዚህ ዓመተ ምህረት አዲስ አበባ እንዲህ ነበረች?“ ብለው እንዲጠይቁና እንዲደነቁ ያደርጋቸዋል።

ይህ የሚያሳየው የኮሪደር ልማቱ ያመጣው ትልቁ ስኬት ቁሳዊ ለውጥ ብቻ ሳይሆን፣ የማህበረሰቡን ስነ- ልቦና ማደሱ ነው። ሰዎች በከተማቸው እንዲኮሩ፣ ኃይማኖታዊ ስርዓታቸውን በክብርና በውበት እንዲያከብሩ እድል ሰጥቷል። በአጭሩ፣ በአዲስ አበባ ውብ ጎዳናዎች ላይ ታቦት ማጀብና ያንን ቅጽበት በፎቶ ማኖር፡ መንፈሳዊ እርካታን፣ የውበት አድናቆትን እና  የማይረሳ የታሪክ ትውስታን በአንድ ላይ ለማግኘት ያስችላል ይላል የፎቶ ግራፍ ባለሙያው ሙሉቀን፡፡

በአጠቃላይ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አዲስ አበባን የጥበብና የውበት መድረክ ጭምር አድርገዋታል። ፋውንቴኖቹ፣ አበቦቹና ዘመናዊው የመንገድ ዳር ግንባታዎች የከተማዋን ነዋሪዎች የስነ-ልቦና እርካታ ከመጨመር ባለፈ፣ የፎቶ ግራፍ ጥበብ እንዲያብብ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ነው። ይህ ውበት ዘላቂ እንዲሆን ደግሞ የመንገዶችን፣ የመዝናኛ ስፍራዎችን፣ የአበቦችንና የፋውንቴኖችን ውበት ጠብቆ ማቆየት የሁሉም ኃላፊነት ነው፡፡

በጊዜው አማረ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review