የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ከጎልደን ግሩፕ ሆስፒታሊቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው ሀገር በቀል የሥነ-ምግብ (ጋስትሮኖሚ) ቱሪዝም ኤክስፖ በሚሊኒየም አዳራሽ በይፋ ተከፍቷል።
በመክፈቻው ላይ የተገኙትሽየቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ እንደገና አበባ የመጀመሪያው የጋስትሮኖሚ ፌስቲቫል የኢትዮጵያን የምግብ ባሕልና እሴት ለመጠበቅ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ በበኩላቸው፣ የቱሪዝም ዘርፍ ለዓለም ኢኮኖሚ ከሚሰጠው አስተዋጽዖ ባለፈ ለኢትዮጵያም ከአምስቱ ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶዎች አንዱ መሆን ችሏል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በተፈጥሮና በታሪክ መስሕቦች የታወቀች ብትሆንም፣ በምግብ ዝግጅት ረገድ ያላትን ዕምቅ ሀብት በሚፈለገው ልክ ጥቅም ላይ እንዳልዋለ ተናግረዋል።
ዘርፉ ወደፊት ኢትዮጵያን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረውም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሼፎች ማኅበር ፕሬዝዳንት እና የጎልደን ግሩፕ ሆስፒታሊቲ መስራች ሼፍ ሄኖክ ዘሪሁን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው ፌስቲቫሉ ዋና ዓላማው የኢትዮጵያን የምግብ ጥበብ ለዓለም ማስተዋወቅና ዝግጅቱን ራሱን የቻለ የቱሪስት መስሕብ ማድረግ መሆኑን ገልጸዋል።
ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚህ ልዩ የጋስትሮኖሚ ፌስቲቫል ላይ የባሕል ምግቦች ለጎብኝዎች በተለያዩ መልኩ የቀረቡ ሲሆን፣ በዘርፉ የተሰማሩ ባለሙያዎችን በማገናኘትና ሀገር በቀል የምግብ ዝግጅት ዕውቀቶችን በማሳደግ የኢኮኖሚ ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ የዝግጅቱ ግብ መሆኑ በመክፈቻ መርሐ ግብሩ ላይ ተገልጿል።
በመሐመድ ኑርዓሊ