በአማራ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት(አፋሕድ) መካከል የተደረሰውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ

You are currently viewing በአማራ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት(አፋሕድ) መካከል የተደረሰውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል ስምምነት ተፈረመ
  • Post category:ፖለቲካ

AMN ጥር 14/2018 ዓ.ም

በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት(አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የማስፈፀሚያ ስምምነት ስርዓት ተካሄደ፡፡

የአማራ ክልል መንግስት ከአፋህድ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ያደረገውን ስምምነት ተከትሎ አመራሮች በርካታ አባላቶቻቸውን በመያዝ ወደ ሠላም መምጣታቸው ይታወቃል።

ይሕን በአፍሪካ ህብረት እና በኢጋድ አደራዳሪነት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት(አፋሕድ) መካከል የተደረገውን የዘላቂ ሰላም ስምምነት የበለጠ ውጤታማ ለማድረግ የሚያስችል የማስፈፀሚያ ስምምነት ስርዓት ተካሂዷል።

በስምምነት ስርዓቱ ላይ የተገኙት የሰላም ሚኒስትር አቶ መሀመድ እድሪስ በመንግሥት የቀረበውን የሰላም ጥሪ ተቀብለዉ ለሕዝባችን ሰላም ለመስጠት ከድሕነት ለመውጣት በሚደረገው ርብርብ በጋራ ለመስራት ወስነው በመምጣታቸው ሊመሰገኑ ይገባል ብለዋል።

ሀገራችን ኢትዮጵያ ካሳለፍናቸው የፖለቲካ ሁኔታ አንፃር ብዙ ያልፈታናቸው ጥያቄዎች ሊኖሩ ይችላሉ ይሕን ክፍተቶች በሰላማዊ መንገድ በጋራ ልንፈታቸው ይገባል ብለዋል።

የአፋህድ ምክትል ሊቀመንበር እና ወታደራዊ አመራር ኮሎኔል ፈንታው ሙሀባ የሰላም አማራጭን የተቀበልነው በምክንያትነት ነው ብለዋል።

የአማራ ሕዝብ ተደራራቢ ጦርነቶች የተካሄዱበት በመሆኑ ዛሬ ላይ ጦርነትን የመሸከም አቅም የለውም ያሉት ኮሎኔል የተነሳንለት ትግል በሕወሃት በሻቢያና በግብፅ በመጠለፍና ከእነዚህ ኃይሎች ጋር በመሆን የአማራም ሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ መፍታት ስለማንችል ሰላማዊ የትግል መንገዱን መርጠናል ብለዋል።

በትግሉ ውስጥ የአማራን ሕዝብም ሆነ ኢትዮጵያዊነትን የማይመጥን አክራሪ ብሄርተኝነት መኖሩን ያነሱት ፋንታሁን ሙሃቤ ሀገሪቱ እንዳትረጋጋና እንድትፈርስ ግን አንፈልግም ብለዋል።

ሌላው የድርጅቱ ወታደራዊ መምሪያ ኃላፊ እያሱ አባተ (ዶ/ር) አፋሕድ ለአንድ አመት ያክል የቆየ ድርድር ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው በሰላማዊ መንገድ የአማራን ሕዝብ ጥያቄና ጥቅም ለማስከበር መከፈል ያለበትን መስዋዕትነት እንከፍላለን ሲሉ ተናግረዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብዱ ሁሴን በበኩላቸው አሁን የተካሄደው ስምምነት ከሕዳር 25 /2018 ዓ.ም የቀጠለ መሆኑን ገልፀው ስምምነቱ የበለጠ ወደ መሬት ለማውረድ ያስችለናል ብለዋል።

ስምምነቱ በግጭቱ የተከሰቱ ሁለንተናዊ ጉስቁልናና ጉዳትን ለመካስ የሚያስችል ስምምነት መሆኑን ያነሱት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ የተሸረሸረውን የሕዝቡን እምነት ለመመለስም ያስችላል ብለዋል።

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review