የተሰሩት የልማት ስራዎች የከተማዋን ዓለም አቀፍ ገፅታ ያሳደጉና የሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው

You are currently viewing የተሰሩት የልማት ስራዎች የከተማዋን ዓለም አቀፍ ገፅታ ያሳደጉና የሁሉንም ዜጋ ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ናቸው

AMN – ጥር 15/2018 ዓ.ም

የአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት ከፍተኛ አመራሮች እና የስራ አስፈፃሚ አባላት የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ የልማት ስራዎችን ጎብኝተዋል::

በአፍሪካ ህብረት እና በኢጋድ አደራዳሪነት በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስትና በአማራ ፋኖ ሕዝባዊ ድርጅት (አፋሕድ) መካከል የዘላቂ ሰላም ስምምነት መካሄዱ ይታወሳል።

በሰላም ስምምነቱ መሠረት ወደ ሰላማዊ ትግል መድረክ የመጡ የአፋሕድ ከፍተኛ አመራሮችና የስራ አስፈፃሚ አባላት የአድዋ ድል መታሰቢያን ጨምሮ በአዲስ አበባ ከተማ የተሰሩ ሰው ተኮር የልማት ስራዎችን እንዲሁም የኮሪደርና የወንዝና ወንዞች ዳርቻ ልማትን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ላይ ያነጋገርናቸው የአፋህድ የውጪ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊና የስራ አስፈፃሚ አባል መቶ አለቃ ማስረሻ ሰጤ በከተማዋ የተከናወኑ የልማት ስራዎች ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚነት ያረጋገጡ ሆነው እንዳገኟቸው ተናግረዋል።

የውጪ ጉዳይ መምሪያ ኃላፊው አያይዘውም ልማቱ የቅርስና ታሪካዊ ቦታዎችን የጠበቀ እንዲሁም ታሪካዊ ስፍራዎች ከነበራቸውን ደረጃ ከፍ ያደረገና የመዝናኛ አማራጭም ጭምር ሆነው መሰራታቸውን ተመልክተናል ብለዋል።

ሌላው የድርጅቱ ምክትል ወታደራዊ አዛዥ ረዳት ፕሮፌሰር እያሱ አባተ በከተማዋ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወኑ የልማት ስራዎች አስደናቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በግጭት ውስጥ ሆኖ ይሕን መሰል የልማት ሥራዎችን በስኬት ማከናወን ከተቻለ በሰላምና ምሉዑ መረጋጋት ውስጥ ቢሆን የበለጡ ስኬቶችን ማየት እንችል ነበረ ሲሉ በቁጭት ተናግረዋል።

ሌሎች የድርጅቱ የስራ አስፈፃሚ አባላትም በከተማዋ በፍጥነት የተከናወኑ የልማት ስራዎች እውነትም ሰው ተኮር የልማት ውጤቶች መሆናቸውን እንዳረጋገጡና የከተማዋን ዓለም አቀፍ ገፅታ ማሳደግ ያስቻሉ ናቸው ሲሉም ተናግረዋል።

የልማት ስራዎቹ ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ታሳቢ ያደረጉ መሆናቸው ደግሞ ይበልጥ አስገራሚ እንደሆነባቸው የገለፁት የስራ አስፈፃሚ አባላቱ ጫካ እያሉ ይነገራቸው ከነበረው ሀሰተኛ መረጃ ይልቅ በጉብኝቱ አዲስ አበባ ከተማ እንደ አዲስ እየተሰራች እንደሆነ መመልከት ችለናል ብለዋል።

በተካሄደው ስምምነት መሰረትም ለሀገራዊ ሰላም መረጋጋትና ልማት በጋራ ከመንግስት ጋር እንደሚሰሩም የድርጅቱ ከፍተኛ አመራሮችና የስራ አስፈፃሚ አባላት አረጋግጠዋል።

በታምሩ ደምሴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review