AMN ጥር 16 ቀን 2018 ዓ.ም
የ23ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ መርሐግብር ዛሬ በሚከናወኑ አምስት ጨዋታዎች ይጀምራል።
በዕለቱ ሊቨርፑል በቪታሊቲ ስታዲየም ምሽት 2:30 ቦርንማውዝን የሚገጥምበት ጨዋታ ይጠበቃል። ሊቨርፑል በሜዳው አንፊልድ በኖቲንግሃም 3ለ0 ከተሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው 10 ጨዋታዎች አንድም ሽንፈት አልገጠመው። የመርሲሳይዱ ክለብ ትልቁ ችግር በአቻ ውጤት ያጠናቀቃቸው ጨዋታዎች መብዛታቸው ነው።
የአርነ ስሎቱ ቡድን የመጨረሻ አራት የሊግ ጨዋታዎቹን ነጥብ በመጋራት አጠናቋል። በተለይ ባሳለፍነው ቅዳሜ ወራጅ ቀጠና ከሚገኘው በርንሌይ ጋር በአንፊልድ 1ለ1 መለያየቱ ደጋፊዎችን አላስደሰተም።

በውድድር ዓመቱ አስደናቂ ጅማሮ ያደረገው ቦርንማውዝ አሁን ላይ ተቸግሯል። ከሳምንታት በፊት ተፅዕኖ ፈጣሪ ተጫዋቹ አንቷን ሴሜንዮን ያጣው ቦርንማውዝ ከመጨረሻ 13 የሊግ ጨዋታ ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው።
በሌሎች የዛሬ ጨዋታዎች ማንችስተር ሲቲ በሜዳው ኢትሃድ ስታዲየም የደረጃው ግርጌ ላይ የሚገኘው ዎልቭስን ምሽት 12 ሰዓት ያስተናግዳል። ሲቲ በመጨረሻ ካደረጋቸው አራት የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች ሦስቱን አቻ ተለያይቶ በአንዱ ተሸንፏል። ይህም ሽንፈት ባሳለፍነው እሁድ በማንችስተር ደርቢ በዩናይትድ የደረሰበት ነው።

በሳምንቱ አጋማሽ በቻምፒየንስ ሊጉም በቦዶ ግሊምት የተረታው ሲቲ በዛሬው ጨዋታ ዎልቭስን ካሸነፈ ነገ አርሰናል እስኪጫወት የነጥብ ልዩነቱን ወደ አራት ያጠባል። የተከላካይ ክፍሉ በጉዳት የሳሳበት ፔፕ ጋርዲዮላ በዛሬው ጨዋታ አዲስ ፈራሚው ማርክ ገሂን ያሰልፋል ተብሎ ይጠበቃል።
በርንሌይ ከቶተንሃም ሆትስፐርስ እንዲሁም ፉልሃም ከብራይተን በተመሳሳይ ምሽት 12 ሰዓት ጨዋታቸውን ይጀምራሉ። 9:30 ሲል ዌስትሃም ዩናይትድ ከ ሰንደርላንድ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል።
በሸዋንግዛው ግርማ