የአፍሪካ ህብረት ከነፃነት ተጋድሎ እስከ አጀንዳ 2063

You are currently viewing የአፍሪካ ህብረት ከነፃነት ተጋድሎ እስከ አጀንዳ 2063

AMN – ጥር 19/2018 ዓ/ም

የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት፣ የአሁኑ የአፍሪካ ህብረት አህጉሪቱን ከባርነትና ከዘር መድልዎ ቀንበር ፈልቅቆ ለማውጣት በነበረው ትልቅ ራዕይ በአዲስ አበባ ከተመሰረተ ስልሳ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል።

ድርጅቱ በእነዚህ ረጅም ዓመታት ውስጥ በርካታ ወርቃማ ስኬቶችን ማስመዝገቡ የሚነገርለት ሲሆን፣ አሁንም ድረስ ግን በብዙ ፈተናዎችና ተስፋዎች መካከል ይገኛል።

በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት፣ ድርጅቱ ከመጀመሪያው የአላማ ለውጥ በማድረግና አዳዲስ ራዕዮችን በመቅረጽ ረገድ ተሳክቶለታል።

የድርጅቱ የምስረታ ግቦች ግልጽና ታላቅ እንደነበሩ መምህር ሙሉዓለም አስታውሰው፤ አባል ሀገራት በገዛ ሀገራቸው ባይታዋር መሆንንና ከሰውነት በታች መቆጠርን አውግዘው በአንድነት መቆማቸው ትልቁ ድል ነበር ብለዋል።

የታሪክ ተመራማሪ የሆኑት ንጉሱ መኮንን በበኩላቸው ህብረቱ ለአፍሪካዊ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ የሚለውን መርህ በተግባር ለማዋል በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በቡሩንዲ፣ በዳርፉርና በሶማሊያ የተከሰቱ ግጭቶችን ለመፍታት ሰራዊት እስከማሰማራት ደርሶ እንደነበረም አውስተዋል፡፡

በተለይም በናይጄሪያ ተከስቶ የነበረውን የቢያፍራ ግዛት የመገንጠል ጥያቄ ለመፍታትና ናይጄሪያን ከመበታተን ለማዳን ቀዳማዊ አፄ ኃይለስላሴ የተጫወቱት ሚና የአፍሪካውያንን የመታረቅ አቅም ያሳየ የታሪክ አሻራ እንደነበር ገልፀዋል።

አሁንም ህብረቱ አፍሪካን በፖለቲካና በኢኮኖሚ የማስተሳሰር ግብን የያዘውን “አጀንዳ 2063” እውን ለማድረግ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል።

አህጉሪቱ ያላት ከአንድ ነጥብ ሦስት ቢሊዮን በላይ ህዝብ፣ ሰፊ የተፈጥሮ ሀብትና በወጣቶች የተሞላ የሰው ኃይል ለወደፊቱ ትልቅ ተስፋ የሚሰጡ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ከዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ አንፃርም በአንዳንድ ሀገራት የሚታዩ አበረታች እንቅስቃሴዎች አህጉሪቱ በዓለም አቀፍ መድረክ እኩል ተወዳዳሪና ተፅዕኖ ፈጣሪ እንድትሆን ዕድል እንደሚፈጥርላት ይጠበቃል ነው ያሉት ንጉሱ መኮንን።

ይሁን እንጂ ድርጅቱ አሁንም ያልተሻገራቸውና እንደ ስጋት የሚታዩ ደካማ የዲሞክራሲ ስርዓቶች፣ ቀጣይነት ያላቸው ግጭቶችና የመልካም አስተዳደር ችግሮች አሁንም ተግዳሮት ሆነው ቀጥለዋል።

መምህር ሙሉዓለም ኃይለማርያም እንደሚገልጹት፣ እነዚህን ስጋቶችን ወደ ዕድል ለመቀየርና ጠንካራ አህጉርን ለመገንባት በመጀመሪያ የአባል ሀገራት መሪዎች ወደ ራሳቸው መመልከትና የቤት ስራቸውን በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

በተለይም ተስፋዎችን ወደ ተግባር ለመለወጥ የላቀ የፖለቲካ ቁርጠኝነት አስፈላጊ ሲሆን፣ ከውጭ ጣልቃ ገብነት ራስን በመከላከል የኢኮኖሚና የፖለቲካ አሰላለፍን ማስተካከል የህብረቱ ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን እንደሚገባ ገልፀዋል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review