AMN-ጥር 20/2018 ዓ.ም
የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ተገልጋዩ በነፃነት ያለ እንግልት አገልግሎት የሚያገኝበት ማዕከል ነው ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች ገለፁ።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር አመራሮች የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ጎብኝተዋል።
አዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግስት አገልግሎት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በተገኙበት የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በአዲስ አበባ ደረጃ ጳጉሜን 5 ቀን 2017 ዓ.ም በይፋ ወደ አገልግሎት መግባቱ ይታወሳል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖልጂ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አመራሮችም ተቋሙን ጎብኝተዋል።

በጉብኝታቸውም የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዜጎች በነፃነት አገልግሎት ያለ ምንም እንግልት የሚስተናገዱበትና የሚያገኝበት ቦታ ነው ብለዋል።
በጉብኝቱ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ማዕከሉ በአደረጃጀትም፣ በአሰራር ስርዓት እንዲሁም በሥነ-ምግባር አርአያ የሆኑ ሰራተኞች እና ጠንካራ የአሰራር ስርዓት ያየንበት ነው ብለዋል።
የአዲስ መሶብ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ አለማየሁ፣የመሶብ አገልግሎት መጀመር የተገልጋይን እንግልት ለመቀነስ፣ የሚያባክነውን ጊዜ ለመቆጠብ እና ህብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ቅሬታ ያነሳባቸው የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በተቋሙ ስር ያሉት አሥራ ሦስት ተቋማት የሲቪል ምዝገባ እና ኢኮኖሚ ዘርፍን ጨምሮ በሶስት ዘርፎች መደራጀታቸውን የገለጹት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በወረዳና በክፍለ ከተማ የሚሰጡ አገልግሎቶች እንደተጠበቁ ሆነው ከአንድ በላይ አገልግሎቶችን ማግኘት ለሚፈልግ ተገልጋይ ቀልጣፋ አገልግሎቶችን ለመስጠት የሚያስችል መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ሰራተኞችም መልካም ሥነ-ምግባር ያላቸውና ጠበቅ ያለ የሥነ-ምግባር መመሪያ እንዲከተሉ የሚገደዱበት ሆኖ መደራጀቱንም ነው ያብራሩት፡፡
በጉብኝቱ የኢኖቬሽን ና ቴክኖሎጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር በለጠ ሞላን ጨምሮ የተቋሙ ከፍተኛ አመራሮች የአዲስ መሶብ የአንድ ማዕከልን አገልግሎት ተገኝተዋል።
በመሀመድኑር አሊ