AMN ጥር 20 ቀን 2018 ዓ.ም
ትዕግስት አሰፋ በለንደን ማራቶን እንደምትሳተፍ አዘጋጆቹ አረጋግጠዋል። የባለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ ትዕግስት በዘንድሮ ውድድር ከባድ ተፎካካሪዎች ይጠብቋታል።
ለኔዘርላንድስ የምትሮጠው የኦሊምፒክ የማራቶን አሸናፊዋ ሲፋን ሃሰን ፣ ኬንያውያኑ ፔርስ ጄፕቺርቺር ፣ ጆይስሊን ጄብጎስኪ እና ሄለን ኦብሪ ተጠባቂ አትሌቶች ናቸው።
ትዕግስት አሰፋ ከ2022 በኋላ ዓለም ላይ ካሉ ምርጥ የማራቶን ሯጮች መሀከል አንዷ ሆናለች። ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ሁለት ጊዜ በበርሊን ማራቶን ስትነግስ ፣ የለንደን ማራቶንንም አንድ ጊዜ በቀዳሚነት ጨርሳለች ።
ሀገሯን በወከለችባቸው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና እና ኦሊምፒክ የብር ሜዳልያ አስገኝታለች።
በበርሊን በነበራት ማራቶን 2:11:53 በመግባት ሰዓቱ እስኪሻሻል ድረስ የዓለም ክብረወሰንን በእጇ አስገብታ እንደነበር ይታወሳል።
ከዚህ ውጪ በለንደን ማራቶን በሴት አሯሯጮች ብቻ ያስመዘገበችው 2:15:50 የዓለም ክብረወሰን ሆኖ ተመዝግቦላታል።
በመጨረሻ ካደረገቻቸው ስድስት ማራቶኖች ከ2ኛ ደረጃ በታች አልጨረሰችም።
ዘንድሮ ሚያዚያ ወር ላይ በሚደረገው የለንደን ማራቶን ላይም ትዕግስት አሰፋ የማሸነፍ ቅድሚያ ግምት ካገኙ አትሌቶች መሀከል አንዷ ሆናለች።
ከትዕግስት ውጪ ደጊቱ አዝመራው እና ባለምላይ ሹመት በውድድሩ የሚካፈሉ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ናቸው።
በሸዋንግዛው ግርማ