የዲጂታሉ ዓለም እስረኞች ፤ ማህበራዊ ሚዲያን ለዕድገት ወይስ ለድብርት ይጠቀሙታል?

You are currently viewing የዲጂታሉ ዓለም እስረኞች ፤ ማህበራዊ ሚዲያን ለዕድገት ወይስ ለድብርት ይጠቀሙታል?
  • Post category:ዲጂታል

AMN – ጥር 21/2018 ዓ.ም

በአሁኑ የሥልጣኔ ዘመን ማህበራዊ ሚዲያ ለሥራና ለዕድገት ያለው ፋይዳ የማይካድ ቢሆንም፣ አጠቃቀማችን ሚዛኑን ሲስት ግን ለከፋ የስነ-ልቦና ቀውስ እየዳረገን ይገኛል። ብዙዎቻችን የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ከመሆን ይልቅ የቴክኖሎጂው “ጥገኛ” እየሆኑ መጥተዋል፤ ይህ ደግሞ በዝምታ የሚሰነዘር የአእምሮ ጤና ስጋት እየሆነ ነው።

ብዙዎች ሶሻል ሚዲያን ዘወትር ካልተከታተሉ አንድ ትልቅ ነገር የሚያመልጣቸው ይመስላቸዋል። FOMO (Fear of Missing Out) ተብሎ የሚጠራው ይህ ስጋት፣ ሰዎች በቀን በአማካይ ከ6 እስከ 7 ሰዓታት በስልካቸው ላይ እንዲተከሉ አድርጓቸዋል።

የስነ-ልቦና ባለሙያዋ ዶክተር ሰላም ዘገየ ከ ኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ ይህ ረዥም ቆይታ ለድብርት እና ለጭንቀት ያጋልጣል። የሚገርመው ደግሞ፣ ሰዎች ከገጠማቸው ድብርት ለመሸሽ ድጋሚ መፍትሄ ፍለጋ ወደ ሶሻል ሚዲያ መመለሳቸው ችግሩን ይበልጥ ውስብስብ እና አዙሪት ያደርገዋል።

ማህበራዊ እና ስነ-ልቦናዊ ቀውሶች

የማህበራዊ ሚዲያ ሱስ፣ በትምህርት እና በሥራ ውጤታማነት ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በማህበራዊ ህይወት ላይም ጥቁር ጥላ ይጥላል። ከቤተሰብ እና ከጓደኞች ጋር አለመግባባት ይፈጥራል።

ሌሎች በሶሻል ሚዲያ የሚያሳዩትን “ፍጹም” ህይወት ከራስ ጋር በማወዳደር “ብቁ አይደለሁም” የሚል የዝቅተኝነት ስሜት ማዳበር እና በራስ መተማመን ማጣት ያስከትላል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ከመኝታ ለመነሳት መቸገር፣ ከሰው ጋር መገናኘት መጥላት እና የግል ንጽህናን እስከ መዘንጋት የሚያደርስ ስነ-ልቦናዊ ስብራት የጤና መቃወስ ችግሮች ያስከትላል።

የወላጆች ኃላፊነት እና የባለሙያ ምክር

ዶክተር ሰላም ጉዳዩን አሳሳቢነት በመጠቆም በተለይ ወላጆች በልጆቻቸው የአእምሮ እድገት ላይ ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው ያሳስባሉ። “ወላጆች ከቁጥጥራቸው ውጭ የሆኑ የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀሞች ታዳጊ ልጆችን ወዴት እንደሚመሯቸው ስለማይታውቅ፣ ልጆች የሚያዩትን ነገር መምረጥ ግዴታ አለባቸው ይላሉ።

ስለዚህ ከ3 ዓመት በላይ የሆኑ ልጆች ፣ በቀን ለ30 ደቂቃ ብቻ (በወላጅ ምርጫ) መጠቀም እንዳለባቸው እና አዋቂዎች ደግሞ የሥራ ባህሪያቸው ካላስገደደዳቸው በስተቀር በቀን ከአንድ ሰዓት ባላይ ባይጠቀሙ ይመከራል ብለዋል።

መፍትሄው

ከዚህ የዲጂታል እስራት ለመውጣት ራስን ማወቅ ዋነኛው መፍትሄ ነው የሚሉት ዶክተር ሰላም፤ ሰዎች ራሳቸውን ሲያውቁ ምን አይነት ነገሮች እንደሚረብሹአቸው እና ምን እንደሚወዱ ይረዳሉ። ከሌሎች ሰዎች ‘ላይክ’ እና ፍቅርን ከመለመን ይልቅ ራሳቸውን መውደድ ይጀምራሉ ብለዋል።

“ዓለም በእድል እና በፈተና መካከል ናት” የሚሉት ዶክተሯ፣ ፈተናው ሲበዛ በመማረር እድሎችን እንዳጡ እንደሚያስቡ ይገልጻሉ፡፡ ሚዛናዊ መሆን ይገባል ሰዎች ለራሳቸው በቂ ጊዜ በመስጠት እና የሶሻል ሚዲያ አጠቃቀማቸውን በመገደብ የአእምሮ ጤናቸውን እንዲጠብቁ ያደርጋል ይላሉ ።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review