AMN- ግንቦት 7/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የተመዘገበው ሁለንተናዊ ልማት አካታች እና ሰው ተኮር ነው ሲሉ “THE REMAKING OF ADDIS ABABA” መፅሐፍ ጸሐፊዎች ገለፁ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እና ሌሎች የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች የአዲስ አበባን የለውጥ ጉዞ በተመለከተ በዓለም አቀፍ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተጻፈውን “THE REMAKING OF ADDIS ABABA” የተሰኘውን መፅሐፍ መርቀዋል።
የመጽሐፉ አርታኢ የሆኑት ፕሮፌሰር ሳይመን ሊ እንደተናገሩት፤ ከዚህ ቀደም እ.ኤ.አ በ2008 እና በ2014 ወደ ኢትዮጵያ በመጡበት ወቅት የተመለከቷት አዲስ አበባና በአሁኑ ወቅት ያለችውን ማነጻጸር አይቻልም።

ባለፉት ዓመታት በአዲስ አበባ የታየው ለውጥ ፈጣንና አስደናቂ ነው ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
በከተማዋ የተከናወኑትን የኮሪደር ልማቶች ያደነቁት ፕሮፌሰር ሳይመን፤ ይህ ለውጥ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በአፍሪካና በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚደነቅ መሆኑን ጠቁመዋል።
“ተስፋ ማድረግ ማለት ዝም ብሎ ማለም ሳይሆን፣ ሕልምን ወደ እውነታ መለወጥ ነው” የሚለውን ታዋቂ አባባል የጠቀሱት ፕሮፌሰሩ፤ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ እየታየ ያለው ተጨባጭ እውነታ የራዕይ ውጤት መሆኑን ተናግረዋል።
በዓለም ዙሪያ ያሉ ጎብኚዎች በመስከረም ወር የሚከበረውን የኢትዮጵያን አዲስ ዓመት በዓል ወደ አዲስ አበባ በመምጣት እንዲያከብሩም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
ከመጽሐፉ ዋና ጸሐፊዎች መካከል ሂርጶ ኩምቢ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ አጠቃላይ ኢትዮጵያንና አዲስ አበባን እያሻገረ ያለው ለውጥ ፍጹም አጠቃላይ፣ ማንም ወደኋላ የማይቀርበትና ሰብዓዊነትን ቅድሚያ የሰጠ መሆኑን ገልፀዋል።
ለመጽሐፉ መዘጋጀት ሦስት ጋዜጠኞችንና አምስት የዶክትሬት ዲግሪ ያላቸውን ምሁራን ጨምሮ በአጠቃላይ ስምንት ሰዎች መሳተፋቸውን ጠቁመው፤ ጥናቱ ፍጹም ገለልተኛና እውነተኛ እይታን የያዘ መሆኑን አስረድተዋል።

ቡድኑ ባካሄደው የምርምር ግኝት መሠረት ለአዲስ አበባና ለሀገሪቷ ትራንስፎርሜሽን መሳካት ሦስት ዋና ዋና ምሰሶዎች ወሳኝ ሚና መጫወታቸውን አብራርተዋል።
የመጀመሪያው ምሰሶ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከፍተኛ የምናብ ራዕይ ማዕከል ያደረገ ሲሆን፤ ይህንን ራዕይ ደግሞ የከተማዋ ከንቲባና በየደረጃው ያሉ አካላት በቁርጠኝነት ወደ መሬት ማውረዳቸው ነው።
ሁለተኛው ምሰሶ የሥራ መሪዎቹ ለሥራ ያላቸው ትጋትና የማይናወጥ ቁርጠኝነት ሲሆን፤ በጥናት ቡድኑ ምልከታና ከሕዝብ በተሰበሰበው ምስክርነት መሠረት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) እና ከንቲባ አዳነች አቤቤ እኩለ ሌሊት ላይ ጭምር በየፕሮጀክት ሳይቶቹ እየተዘዋወሩ ሥራዎችን በቅርበት መከታተላቸው አንስተዋል።
ሦስተኛው ምሰሶ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቢዝነስ ባለቤቶች፣ መሐንዲሶች፣ ወጣቶችና ሴቶች ያሳዩት አስደናቂ የተቀናጀ ትብብር ነው ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ሌላኛው የመጽሀፉ ዋና ጸሐፊ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ዳንኤል ከርሊ በበኩላቸው፤ በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለው ሰብዓዊነትንና የተፈጥሮ ጥበቃን ማዕከል ያደረገ ሁለንተናዊ ልማት ነው ብለዋል።
እንደ ሌማት ትሩፋት፣ የአረንጓዴ አሻራ እና የቀዳማይ ልጅነት ያሉ ፕሮጀክቶች በሰው ልጅ የወደፊት ተስፋ ላይ እምነት ሊያሳድርባቸው እንደቻለ በምስክርነታቸው ገልጸዋል።