AMN- ጥር 21/2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ በከተማዋ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን ለመምራት የወጣውን ደንብና የክፍያ ተመን ተግባራዊነት ላይ ያተኮረ የምክክር መድረክ አካሄደ።
መድረኩ በአተገባበር ሂደት የሚታዩ ክፍተቶችን በመድፈን የተጠያቂነት ሥርዓት በመዘርጋት የህዝቡን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ለመመለስ ያለመ ነው።
በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አዘጋጅነት በተካሄደው በዚህ መድረክ ላይ ከማዕከል እስከ ወረዳ የሚገኙ የዘርፉ አመራሮች ፣ ባለሙያዎች እና የስፖርት ማህበራት ስራ አስፈፃሚዎች ተሳትፈዋል።

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ በላይ ደጀን እንደገለጹት ፤ የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርቱ ዘርፍ በሰጠው ልዩ ትኩረት በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ደረጃቸውን የጠበቁ የማዘውተሪያ ስፍራዎች ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።
ይሁን እንጂ እነዚህን ማዘውተሪያዎች ወጥነት ባለው መልኩ ለማስተዳደር የወጡ ደንቦችና የክፍያ ተመኖች በአግባቡ አለመተግበራቸው ቅሬታዎችን ሲያስነሳ መቆየቱን ጠቁመዋል።
ቢሮው ባካሄደው የቁጥጥር ስራ በየክፍለ ከተሞቹ ወጥነት የጎደለው አሰራር መኖሩን ማረጋገጡን የገለጹት ኃላፊው ፣ ይህ የምክክር መድረክ ስህተቶችን ለማረም እና የጋራ መግባባት ለመፍጠር ታስቦ የተዘጋጀ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ደንቡን ጥሰው በሚገኙና ተደጋጋሚ ጥፋት በሚፈጽሙ አካላት ላይ ጥብቅ አስተዳደራዊ እርምጃ እንደሚወሰድ አስጠንቅቀዋል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ፣ በስራ ሂደት ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች አንስተዋል።
በታምሩ ደምሴ